የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮውን ሊዘጋ እንደሚችል አስጠነቀቀ
ባንኩ ሰራተኞቹ በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች እንደተደበደቡበት ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል
ኢትዮጵያ በበኩሏ የተፈጠረውን ክስተት እንደምትመረምር እና እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃ ነበር
የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮውን ሊዘጋ እንደሚችል አስጠነቀቀ፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ ያሉ ሁለት የባንኩ ሰራተኞች በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች ድብደባ፣ እስር እና እንግልት እንደደረሰባቸው አስታውቆ ነበር።
ባንኩ እንዳለው ሁለት ሰራተኞቹ የቬና የዲልሎማሲ ጥበቃ ስምምነትን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ቢሮ አስተናጋጅ ሀገራት ስምምነትን የጣሰ ክስተት በኢትዮጵያ መፈጸሙንም ገልጿል።
የተፈጠረውን ክስተት ለኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ማመልከቱን የሚገልጸው የአፍሪካ ልማት ባንክ ጉዳዩ መፈጸም እንደሌለበት፣ ህግ መጣሱን እና ጉዳዩ ተመርምሮ እርምጃ እንደሚወሰድ በኢትዮጵያ በኩል ቃል ተገብቶልኛል ሲልም በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡
ባንኩ አሁን ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል በገባው መሰረት በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዳልወሰደ እና ጉዳዩን ስለመመርመሩ መረጃ እንዳልሰጠው ገልጿል፡፡
መንግስት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥያቄን ውድቅ አደረገ
ይህን ተከትሎም ባንኩ የኢትዮጵያ ቢሮውን ሊዘጋ እና ሰራተኞቹንም ወደ ሌላ ሀገራት እንደሚያዘዋውር ገልጿል ሲል ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ "ከአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ቢሮ ጋር የተፈጠረው ክስተት ባንኩ ቢሮውን እንዲዘጋ አላደረገውም፣ የሁለቱ ግንኙነትም አልተቋረጠም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ይሁንና የኢትዮጵያ ጸጥታ ሀይሎች በአፍሪካ ልማት ባንክ የአዲስ አበባ ቢሮ ሰራተኞች ላይ ለምን ድብደባ እንደፈጸሙ ከሁለቱም ወገኖች በኩል በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በፈረንጆቹ 1963 በሱዳን ካርቱም በተካሄደ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተቋሙ እንዲመሰረት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የተቋቋመ አፍሪካዊ ተቋም ነው።
ባንኩ በአዲስ አበባ ያለውን የኢትዮጵያ ቅርንጫፉን በ1967 የከፈተ ሲሆን ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የመሰረተ ልማት፣ ግብርና እና ሌሎች የልማት ስራዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።