መንግስት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥያቄን ውድቅ አደረገ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ለራሱ ስራ ማከናወኛ እንዲጠቀም የሚፈቅድ ህግ እንዲዘጋጅ ጥያቄ አቅርቦ ነበር
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዓመታዊ ትርፌ ላይ የተወሰነውን ለራሴ ካልተጠቀምኩ እቅዴን ለማሳካት እቸገራለሁ ማለቱ ተገልጿል
መንግስት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥያቄን ውድቅ አደረገ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመንግስት የልማት ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ላነሷቸው ጥያቄዎች በምክር ቤቱ ተገኝተው ምላሽ ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ከ60 በላይ ጥያቄዎችን በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጧቸው ለሚንስትሩ አቅርበዋል።
ከተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያም ከመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሚያገኘው ዓመታዊ ትርፍ ውስጥ የተወሰነውን ለራሱ ስራ ማከናወኛ እንዲጠቀም የሚፍቅድ ህግ በረቂቅ አዋጁ ላይ ይካተት የሚለው ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከባንኩ ጋር አደረግነው ባሉት ውይይት ባንኩ በሀገሪቱ ያሉ ሰፊ የመልማት አቅም ለመመለስ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ድጋፍ ለማድረግ እና ወደ ውጪ ሀገራት የሚላኩ ምርቶችን በስፋት እንዲመረቱ ለማገዝ መቋቋሙን ከግምት ውስጥ እንዲገባለት ጥያቄ አቅርቧል ተብሏል፡፡
በመሆኑም የመንግስት የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በየዓመቱ ያገኘውን ትርፍ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ ከሚያደርገው ላይ ሙሉ ለሙሉ አልያም በከፊል ለራሱ እንዲወስድ እንዲፈቀድለት የምክር ቤቱ አባላት ለገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ መንግስት ልማት ባንክ ከነበረበት ኪሳራ እንዲወጣ ላለፉት አምስት ዓመታት የተበላሸ ብድር እንዲስተካከል፣ የበጀት እጥረቱ እንዲፈታ፣ የአሰራር ማሻሻያዎችን ጨምሮ ብዙ ድጋፎችን ሲደርጉ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
አንድ ሰው በሶስት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የቦርድ አመራር እንዲሆን የሚፈቅደው ህግ ጥያቄ ተነሳበት
ባንኩ በተደረገለት ድጋፍ መሰረትም ትርፋማ ሆኗል ያሉት አቶ አህመድ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ የማደርገውን ትርፍ ለራሴ ካልተጠቀምኩ ያሰብኩትን እቅድ ለማሳካት እቸገራለሁ ማለቱ ስህተት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቀጣይም ውጤታማ እንዲሆን መንግስት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ነገር ግን በመንግስት ልማት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በቋሚነት ያገኘውን ትርፍ ለራሱ እንዲወስድ የሚፈቅድ አንቀጽ ሊካተት ግን አይገባም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ ማንኛውም የቦርድ አባል ከሶስት ለማይበልጡ ተወዳዳሪ ላልሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በተመሳሳይ ጊዜ በቦርድ አባልነት በመሾም ሊያገለግል ይችላል በሚል በረቂቅ አዋጁ ላይ መካተቱ የለበትም ሲሉ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡