የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ያሉ ሰራተኞቹ ድብደባና እስር እንደተፈጸመባቸው ገለጸ
ኢትዮጵያ በበኩሏ በባንኩ ሰራተኞች ላይ እንግልት መድረሱን አምና እርምጃ እንደምትወስድ ገልጻለች
በባንኩ ሰራተኞች ላይ ጉዳት እንደሚመረመር እና እርምጃ እንደሚወሰድም ባንኩ ቃል እንደተገባለት አስታውቋል
የአፍሪካ ልማት ባንክ ሰራተኞቹ በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች እንደተደበደቡበት ገለጸ።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ያሉ ሁለት የባንኩ ሰራተኞች በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች ድብደባ፣ እስር እና እንግልት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
ባንኩ እንዳለው ሁለት ሰራተኞቹ የቬና የዲልሎማሲ ጥበቃ ስምምነትን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ቢሮ አስተናጋጅ ሀገራት ስምምነትን የጣሰ ክስተት በኢትዮጵያ መፈጸሙንም ገልጿል።
የተፈጠረውን ክስተት ለኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ማመልከቱን የሚገልጸው የአፍሪካ ልማት ባንክ ጉዳዩ መፈጸም እንደሌለበት፣ ህግ መጣሱን እና ጉዳዩ ተመርምሮ እርምጃ እንደሚወሰድ በኢትዮጵያ በኩል ቃል ተገብቶልኛልም ብሏል።
ባንኩ አክሎም ከኢትዮጵያ ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳለው ገልጾ የተፈጠረው ክስተትም ግንኙነቱን እንደማያበላሽ አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው "ከአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ቢሮ ጋር የተፈጠረው ክስተት ባንኩ ቢሮውን እንዲዘጋ አላደረገውም፣ የሁለቱ ግንኙነትም አልተቋረጠም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ ጸጥታ ሀይሎች በአፍሪካ ልማት ባንክ የአዲስ አበባ ቢሮ ሰራተኞች ላይ ለምን ድብደባ እንደፈጸሙ ከሁለቱም ወገኖች በኩል በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በፈረንጆቹ 1963 በሱዳን ካርቱም በተካሄደ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተቋሙ እንዲመሰረት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የተቋቋመ አፍሪካዊ ተቋም ነው።
ባንኩ በአዲስ አበባ ያለውን የኢትዮጵያ ቅርንጫፉን በ1967 የከፈተ ሲሆን ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የመሰረተ ልማት፣ ግብርና እና ሌሎች የልማት ስራዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።