የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በናይሮቢ ኬንያ ተጀመረ
ጉባዔው ከድርቅ ጀምሮ እስከ በርሃማነት በተደቀነባት የአፍሪካ አህጉር የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ የሚመክር ነው
በጉባዔው ከ20 የሚበልጡ የአፍሪካ መሪዎች፣ የበርካታ ሀገራት ሚንስትሮች፣ ልዑኮችና የአየር ንብረት ተሟጋቾች ይሳተፋሉ
አየር ንብረት መጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ መካሄድ ጀመረ።
ከድርቅ ጀምሮ እስከ በርሃማነት በተደቀነባት የአፍሪካ አህጉር የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ የሚመክር የአየር ንብረት ጉባኤ በናይሮቢ መካሄድ ጀምሯል።
በኬንያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ጉባኤ ከነሀሴ 29 እስከ ጳጉሜ 1 የሚካሄድ ሲሆን፤ ከ20 የሚበልጡ የአፍሪካ መሪዎች፣ የበርካታ ሀገራት ሚንስትሮች፣ ልዑኮችና የአየር ንብረት ተሟጋቾች ይሳተፋሉ።
በአህጉሪቱ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኬንያ ባሉ ሀገራት ከ40 ዓመታት ወዲህ የከፋ የተባለ ድርቅ ተከስቷል። በዚህም በአፍሪካ ቀንድ የምግብ ዋስትና ቀውስ የተከሰተ ሲሆን፤ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ እንስሳት ሞተዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ እንደሚለው እየጨመረ ከመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ አደጋዎች ሀገራት በየዓመቱ ከሰባት እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብታቸውን ያጣሉ። ይህም አሀዝ በጎርጎሮሳዊያኑ 2030 ወደ 50 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል ተብሏል።
በጉባኤው የአፍሪካ መሪዎች ከአየር ንብረት ለውጥ በፍጥነት ማገገምና መቋቋም የሚስችሉ ጥረቶችን ይደግፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አያሌ ባለድርሻ አካላት በጉባኤው መፍትሄና እርምጃ ላይ የሚያተኩሩ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ እየወተወቱ ሲሆን፤ ይህንም አቅፏል የተባለው “የናይሮቢ መግለጫ” በጉባኤው የመጨረሻ ቀን እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።