የአየር ንብረት ለውጥ በግጭት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንደሚያደርግ ተነገረ
የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ገንዘብ እየጠየቁ ነው
ችግር ባለባቸው ሀገራት በግጭት የሚሞቱ ሰዎች በ10 በመቶ ይጨምራል ተብሏል
የዓለም የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የአየር ንብረት ለውጥ ግጭትን እንደሚያባብስ ተናግሯል።
በተለይም በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር እንደሚጨምርና የሀገር ውስጥ ምርትን እንደሚቀንስ ገልጿል።
የዓለም ባንክ በየዓመቱ "የመፍረስ ስጋትና ግጭት የተስፋፋባቸው" ሀገራትን ዝርዝር የሚያወጣ ሲሆን፤ አሁን ላይ 39 ሀገራት በዝርዝሩ አካቷል። ከእነዚህም ውስጥ 21 የአፍሪካ ሀገራት ናቸው።
እስካሁን በባንኩ ዝርዝር ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ 61 ሀገራት ተለይተዋል።
ባንኩ የአየር ንብረት ለውጥ ለግጭት መንስኤ ባይሆንም፤ ግጭት እና እንደ ረሃብና ድህነት ያሉ ችግርችን እንዲባባሱ ግን እያደረገ ነው ብሏል።
አይኤምኤፍ በሪፖርቱ ችግር ባለባቸው ሀገራት በግጭት የሚሞቱ ሰዎች በ2060፤ በ10 በመቶ ከፍ እንደሚችል አስታውቋል።
ከዚህ ባሻገርም ተቋሙ እንዳለው ከሆነ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በ2060፤ በሀገራቱ ተጨማሪ 50 ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ ይዳረጋሉ።
ምንም እንኳ ባለፉት ጥቂት ወራት የአየር ንብረት ለውጥ ማስረጃዎች በዓለም ላይ እየተደራረበ ቢሆንም፤ እርምጃ እንዳይወሰድ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ በኢኮኖሚ ድክመት እየተሸፈነ ነው ተብሏል።
የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ሀብታም ሀገራት ገንዘብ እንዲያቀርቡ እየወተወቱ ነው።