ሳኡዲ አረቢያ እና የአፍሪካ መሪዎች የጋዛው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ
የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ መሀል ባሉ የሀማስ ምሽጎች ላይ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ
የንጉሱ ጥሪ በሪያድ ስብሰባ ላይ በነበሩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የጋራ መግለጫም ላይ ተስተጋብቷል
የሳኡዲው ንጉስ መሀመድ ቢን ሳልማን የጋዛው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
የንጉሱ ጥሪ በሪያድ ስብሰባ ላይ በነበሩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የጋራ መግለጫም ላይ መስተጋባቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
መሀመድ ቢን ሳልሜን በሪያድ በተካሄደው የአፍሪካ- ሳኡዲ ስብሰባ ላይ "በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል ወረራ እየደረሰ ያለውን ጥቃት፣ የንጹሃን ግድያ እና የአለምአቀፍ ህግ ጥሰት እናወግዛለን" ብለዋል።
ንጉሱ አክለውም "ጦርነቱ እና ፍልስጤማውያንን አስገድዶ የማስወጣት ተግባር መቆም አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
በትናንትናው እለት በጋዛ ሆስፒታሎች ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት 27 ሰዎች መገደላቸውን እና በሆስፒታሎች አካባቢ የእግረኛ ጦር ውጊያ መደረጉን የፍልስጤም ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ መሀል ባሉ የሀማስ ምሽጎች ላይ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ።
ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ ያደረሰውን ያልተጠበቀ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እያደረሰች ባለው የመልሶ ማጥቃት ከ11ሺ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በሳኡዲ-አፍሪካ ስብሰባ ላይ የተሳተፋ የአፍሪካ መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ በወረራ በተያዙ የፍልስጤም ግዛቶች ላይ እየተደረገ ያለው ወታደራዊ ዘመቻ እንዲቆም እና ንጹሃን እንዲጠበቁ አሳስበዋል።
አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና በርካታ ሀገራት እስራኤል በጋዛ ተኩስ እንድታቆም ቢጠይቁም፣ እስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ የተኩስ አቁሙን ሀሳብ አይቀበሉትም።