አፍሪካ በ3ኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተፈተነች መሆኑን ተገለጸ
ደቡብ እና ሰሜን አፍሪካ አገራት በሶስተኛው ዙር ወረርሽኝ ክፉኛ እየተጠቁ ነው ተብሏል
እስካሁን ከ150 ሺህ በላይ አፍሪካውያን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል
አፍሪካ በሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተፈተነች መሆኑን የአህጉሪቱ የበሽታዎች መከላከል እና ቁጥጥር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ገለጸ።
ማዕከሉ በድረገጹ ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ዜጎች ቁጥር 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ደርሷል።
በቫይረሱ ከተጠቁት ውስጥም 151 ሺህ 232 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በዚህ በሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁን ላይ የደቡባዊ እና ሰሜናዊ አፍሪካ አገራት ክፉኛ እየተጠቁ ሲሆን ቫይረስ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በመሰራጨት ላይ ነው ተብሏል።
ደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ ጥቃት እየተፈተኑ ካሉ አገራት መካከል ዋነኛዋ ስትሆን እስከዛሬ ድረስ ብቻ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎቭ በኮሮና ቫይረስ ሲጠቁ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ64 ሺህ በላይ ሆኗል።
ሞሮኮ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሁለተኛዋ በኮሮና ቫይረስ የተጠቃች አገር ሰትሆን ከ541 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በዚህ ቫይረስ ተጠቅተዋል።
ቱኒዝያ በሶስተኛው ዙር ክፉኛ በመጠቃት ላይ ያለች አገር ስትሆን ጎረቤቶቿ ድንበራቸውን በመዝጋት ላይ እንደሆኑ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ግብጽ ኢትዮጵያ እና ሊቢያም ቫይረሱ ቀስ በቀስ እየተሰራጨ ያለባቸው አገራት እንደሆኑ የማዕከሉ የማስጠንቀቂያ ሪፖርት ያስረዳል።
እንደ ማዕከሉ መረጃ ከሆነ የአፍሪካ አገራት በየጊዜው ዝርያውን እየቀያረ ባለው የኮሮና ቫይረስ የበለጠ እንዳይጎዱ የምርመራ አቅምን ማሳደግ፤ክትባቶችን ለዜጎቻቸው መስጠት እና ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎችን እንዲወስዱም ማዕከሉ አሳስቧል።
ኮሮና ቫይረስ በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ከታህሳስ 19 ቀን 2019 አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻይና ውሃን ግዛት የተከሰተ ሲሆን አስከዛሬዋ ቀን ድረስ ከ185 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲያዙ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን እንዳጡ የጆን ሆፕኪነስ ዩንቨርሲቲ ዕለታዊ መረጃ ይጠቁማል።