የኮሮና ተጽዕኖ ዘንድሮም ዓለምን እስከ 2.4 ትሪሊዬን ዶላር ሊያሳጣ ይችላል ተባለ
የዓለም ምጣኔ ሃብት ባለፈው ዓመት የወረርሽኙ ምክንያት በ3 በመቶ አሽቆልቁሎ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል
ጫናው በተለይም በአዳጊ ሃገራት ላይ እንደሚበረታም የተመድ ሪፖርት ያትታል
የዓለም ምጣኔ ሃብት የኮሮና ወረርሽኝ በቱሪዝም ሴክተሩ ላይ ባደረሰው ጉዳት ምክንያት እስከ 2.4 ትሪሊዬን ዶላር የሚደርስ ገቢን ልታጣ እንደምትችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ የንግድና የልማት ጉባዔ ተካሂዷል፡፡
ወረርሽኙ በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ የከፋ ጫና ማሳደሩን በጉባዔው በቀረበ ሪፖርት ተገልጿል፡፡
በተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት (2021) ቀደም ሲል ከተገመተው በላይ ከ1.7 እስከ 2.4 ትሪሊዬን ዶላር እንደሚታጣም ነው ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡
ጫናው በተለይም በአዳጊ ሃገራት ላይ ይበረታልም ይላል፤ ኪሳራውን በተለያዩ ሶስት የቢሆን እሳቤዎች (ሴናሪዮስ) ላይ ተመስርቶ ግምቶቹን የሚያስቀምጠው ሪፖርቱ፡፡
የመጀመሪያው ቢሆን የጎብኚዎች ቁጥር በ74 በመቶ ሊቀንስ ቢችል በሚል ግምት የተሰራ ሲሆን ግምቱ እውን ቢሆን የዘርፉ ገቢ በ1 ትሪሊዬን ዶላር ሊቀንስና ይህም ዓለምን እስከ 2.4 ትሪሊዬን ዶላር ሊያሳጣ እንደሚችል ያስቀምጣል እንደ ዘ ናሽናል ዘገባ፡፡
ሁለተኛው ነገሮችን በአዎንታ በመመልከት የጉብኚዎቹ ቁጥር በአማካይ እስከ 63 በመቶ ቢቀንስ በሚል የተሰራ ነው፡፡
በዚህ ግምት መሰረትም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በ695 ቢሊዮን ዶላር ሊቀንስ እና በጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ምጣኔ ላይ የ 1.7 ትሪሊዬን ዶላር ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል ይተነብያል፡፡
ሶስተኛው ቢሆን ደግሞ የሃገራትን የእድገትና የመከተብ አቅም ታሳቢ አድርጎ የተሰራ ነው፡፡
እስካሳለፍነው ግንቦት መጨረሻ ድረስ የህዝባቸውን 50 በመቶ ለመከተብ የቻሉ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ስፔንና እንግሊዝን መሰል 55 ሃገራት በቶሎ አገግመው የተሻለ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡
ወረርሽኙ ክፉኛ ካደቀቃቸው ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎች መካከል የጉዞና የቱሪዝም ዘርፉ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
በዚህም የዓለም ምጣኔ ሃብት ባለፈው ዓመት በ3 በመቶ አሽቆልቁሎ እንደነበር ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) አስታውቆ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በ6 በመቶ ሊያድጋል እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ዘርፉ እንዲነቃቃና ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ በተለይ በአዳጊ ሃገራት ብዙ መስራት ቢጠበቅም እስከ 2023 ድረስ ተቀዛቅዞ ሊቆይ እንደሚችልም ነው ሪፖርቱ የሚጠቁመው፡፡