በአፍሪካ የተከሰተውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ ለመከላከል የተገኝው የገንዘብ ድጋፍ ከ10 በመቶ በታች ነው ተባለ
እስካሁን ከአለም ጤና ድርጅት እና ከተለያዩ ለጋሽ አካላት የተገኝው ገንዘብ 20 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ስርጭት አሁን በሚገኝበት ደረጃ አፍሪካ 10 ሚሊየን ዶዝ ክትባት ያስፈልጋታል
በአፍሪካ የተከሰተውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤም ፖክስ) ስርጭትን ለመከላከል እየተደረገ የሚገኝው ጥረት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት የአፍሪካ ሲዲስ አስታወቀ።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ስርጭቱ እየጨመረ የመጣውን በሽታ ለመቆጣጠር የሚገኝው የፈንድ ድጋፍ ከከትባት ውድነት ጋር ተያይዞ እክል እንደፈተረበት ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በሽታውን ለመከላከል አጠቃላይ ከሚያስፈልገው 245 ሚሊየን ዶላር 10 በመቶውን ወይም 20 ሚሊየን ዶላር ብቻ ማግኝቱን ያስታወቀው ድርጅቱ፤ ተጨማሪ የገንዘብ እና የክትባት ድጋፎችን በአፋጣኝ ማግኝት ካልተቻለ ስርጭቱ ሊከፋ እንደሚችል አሳስቧል፡፡
የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ሃላፊ ንጋሽ ንጎንጎ “በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ ህብረት እና ከኮንጎ መንግስት ካግኝነው 20 ሚሊየን ዶላር እየተንቀሳቀስን እንገኛለን በሽታው እየሄደበት ከሚገኝው የስርጨት መጠን አንጻር ይህ እጅግ ዝቅተኛ ነው” ብለዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ጄን ካሴያ በበኩላቸው አንድ ሚሊየን ዶዝ ክትባቶችን በድጋፍ መልክ ለማግኝት የአፍሪካ ሲሰዲሲ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ፈረንሳይ ፣ ጀርመን እና ስፔን ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት መካከል ሲሆኑ ሌሎች ክትባት አምራቾች እና ሀገራት ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርጉ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
የአውሮፓ ህብረት እና የኔዘርላንዱ የክትባት አምራች ባቫሪያን ኖርዲክ ለአፍሪካ የክትባት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
በጦርነት እየታመሰች ከምተገኝው ዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ተነስቶ ሌሎች የአህጉሪቷን ሀገራት እያዳረሰ የሚገኝው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በአለም ጤና ድርጅት ማህበረሰባዊ የጤና ስጋት ስለመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ ታውጇል፡፡
አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ስርጭቱ በሚገኝበት ደረጃ በአጠቃላይ 10 ሚሊየን ዶዝ ክትባት እንደሚያስፈልጋት ያስነበበው ሮይተርስ የክትባቱ ዋጋ ውድነት ፈተና መደቀኑን ዘግቧል፡፡
የክትባቱ አምራቾች በአሁኑ ወቅት የአንድ ዶዝ ክትባት ዋጋ 100 ዶላር ተምነው በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡