የአለም ጤና ድርጅት ስርጭቱ እየጨመረ በመጣው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዙርያ አስቸኳይ ጉባኤ ጠራ
ጉባኤው የበሽታው ስርጭት የአለም አቀፍ ስጋት የመሆኑን ደረጃ ለመወሰን የሚካሄድ ነው
የዝንጅሮ ፈንጣጣ በአሁኑ ወቅት ጎረቤት ኬንያን ጨምሮ በአምስት የአፍሪካ ሀገራት መከሰቱ ተረጋግጧል
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ስርጭቱ እየጨመረ በሚገኘው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ዙርያ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል፡፡
ጉባኤው በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው ወረርሽኝ በአለም አቀፍ ደረጃ ስጋት የመሆኑን ደረጃ ለመወሰን የሚካሄድ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ከ2023 ጀምሮ በዲአር ኮንጎ የተከሰተው በሽታው እስካሁን 27 ሺህ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን ከ1100 በላይ ሰዎችን ህይወት ነጥቋል፡፡
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተጨማሪ 50 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ያረጋገጠው የአለም ጤና ድርጅት ብሩንዲ ፣ ኬንያ ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ በሽታው የታየባቸው ሀገራት ናቸው ብሏል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም በአሁኑ ወቅት በአምስት የአፍሪካ ሀገራት የተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወደ አጎራባች ሀገራት እና ከአፍሪካም ተሻግሮ በሌሎች የአለም ክፍሎች የሚከሰትበት እድል ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በበሽታው የስርጭት ሁኔታ ላይ ለመምከር ዳይሬክተሩ በጠሩት ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ አለም አቀፍ የጤና ባለሙያዎች የተካተቱበት አስቸኳይ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፤ ባለሙያዎቹ የበሽታውን ወቅታዊ የስርጭት ሁኔታ በመገምገም አለም አቀፍ ስጋት የመሆኑን መጠን ቴክኒካዊ ምክር ለድርጅቱ እንዲሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡
ጉባኤውን ለማካሄድ የተቆረጠለትን ቀን ይፋ ያላደረገው የአለም ጤና ድርጅት ከጉባኤው በኋላ የበሽታውን የስጋት ደረጃ እንደሚያሳውቅ ተናግሯል፡፡
ዶክተር ቴዎድሮስ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ 1 ሚሊየን ዶላር በመበጀት ስርጭቱ በከፋባቸው ዲአር ኮንጎ እና አጎራባች ሀገራት በሽታውን ለመከላከል እንዲሁም ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በቅርቡ የተመረቱ ሁለት ክትባቶች ባሳለፍነው ሰኔ በኮንጎ መንግስት ፈቃድ አግኝተው ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሽታው ከዚህ ቀድም ከሚታወቅብት ህዋስ ክሌድ ኤቢ የሚባል ልውጥ ህዋስ መፍጠሩ የተሰማ ሲሆን ይህኛው የበሽታው ዝርያ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ እንደሚተላለፍ እና የመገደል አቅሙም ከፍተኛ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
በ2022 በተለያዩ ሀገራት በሰፊው ስርጭቱ እየጨመረ የነበረው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ባሳለፍነው አመት ግንቦት ወር ላይ ዓለም አቀፍ አጣዳፊ የጤና ስጋት መሆኑ ማብቃቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ የጀርባ ሕመም እና የጡንቻ ሕመም ከበሽታው ምልክቶች መካከል ናቸው።
በሽታው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በነበረበት ወቅት በ111 አገራት 87,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 140 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡