የዓለም ጤና ድርጅት፤ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋ አይደለም አለ
ከሰሞኑ 30 ገደማ ሳይንቲስቶች "ሞንኪ ፖክስ" የሚለው ስያሜ እንዲቀየር መጠየቃቸው የሚታወስ ነው
ድርጅቱ ሆኖም በሽታው የቅርብ ክትትልን የሚፈልግ ነው ብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት፤ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Monkeypox) ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋ አይደለም አለ፡፡
የድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ የጤና አደጋዎች አማካሪ ኮሚቴ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዓለምን የሚያሰጋ ጉዳይ እንዳይደለ አስታውቋል።
ኮሚቴውን ለድንገተኛ ስብሰባ ጠርተው ስለ በሽታው የጠየቁት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምም የኮሚቴውን ውሳኔ ተቀብለዋል።
በሽታው ያልተለመዱ ሁኔታዎች አሳይቷል ሲል ድርጅቱን ያማከረው ኮሚቴው በአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት መኖሩ ቢታወቅም ችላ መባሉ አግባብ እንዳይደለ በመጠቆም አሁንም የቅርብ ክትትልን የሚሻ ነው ብሏል፡፡
ከሳምንታት በኋላ የስርጭት ሁኔታውንና ጉዳቱን ማጥናት እንደሚገባም ኮሚቴው መክሯል፡፡
የተለያዩ የኮሚቴው አባላት የተለያዩ ሃሳቦችን አንጸባርቀው የነበረ ቢሆንም በስተኋላ በሽታው ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋ አይደለም ሲሉ መስማማታቸውን ድርጅቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የበሽታውን የስርጭት ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቫይረሱ ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋን ደቅኖ እንደሆነ ለማወቅ ኮሚቴው እንዲያማክራቸው ጠይቀዋል፡፡
በሽታው እስካሁን ሪፖርት ወዳልተደረገባቸው ሃገራት ጭምር መዛመቱ አሳሳቢ ነው በሚል ነበር ዶ/ር ቴድሮስ ኮሚቴውን ባሳለፍነው ሃሙስ ለድንገተኛ ስብሰባ የጠሩት፡፡
ሆኖም ኮሚቴው ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋ አይደለም ሲል ሙያዊ ምክረ ሃሳብን ሰጥቷል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ የኮሚቴውን ውሳኔ መቀበላቸውንም ነው ድርጅቱ ያስታወቀው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከአሁን ቀደም ኮሮና፣ ኢቦላ እና ዚካ የተባሉ ከፍተኛ የመተላለፍ አቅም እና ፍጥነት ያላቸው በሽታዎች ባጋጠሙ ጊዜ ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው በሚል ሃገራት ሊያደርጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች የተመለከቱ መመሪያዎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
"ሞንኪ ፖክስ" በ1950ዎቹ በተለያየ ምድብ ተለይተው በዝንጀሮዎች ላይ ሲደረጉ በነበሩ ምርምሮች ነው መኖሩ የታወቀው፡፡ በቫይረሱ የተያዘ የመጀመሪያው ሰው የተገኘውም በ1970ዎቹ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን ከ3 ሺ 200 በላይ ሰዎች ሪፖርት በበሽታው ተይዘዋል፡፡ ኬዙ እስካሁን በሽታው መኖሩን ሪፖርት ባላደረጉ 40 ሃገራት ጭምር የተገኘ ነው እንደ ድርጅቱ ገለጻ፡፡
ከሰሞኑ 30 ገደማ ሳይንቲስቶች "ሞንኪ ፖክስ" የሚለውን ስያሜ እንዲቀይር ድርጅቱን መጠየቃቸው የሚታወስ ነው፡፡