የአፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት የሮማ ሊቀ ጳጳስ ተመሳሳይ ፆታ ጥንዶችን በተመለከተ ያወጡትን አዋጅ ውድቅ አድረጉ
የሮማ ሊቀ ጳጳስ የቤተ ክርስቲያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ መፍቀዳቸው ይታወሳል
የአፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ ያወጡት አዋጅ “ከፈጣሪ ፈቃድ የወጣ ነው” ብለዋል
የአፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት የሮማ ሊቀ ጳጳስ ኣባ ፍራንሲስ ተመሳሳይ ፆታ ጥንዶችን በተመለከተ ያወጡትን አዋጅ ውድቅ አድረጉ።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ከሳምንት በፊት የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቃድ መስጠታቸው ይታወሳል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ አዲሱን የቫቲካን መመሪያ የሚያትቱ መዛግብትን ማፀድቃቸውን ተከትሎ ነበር የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቃድ መስጠታቸው የተሰማው።
ፖፕ ፍራንሲስ፤ የቤተ-ክርስትያኒቱ ቄሶች የተመሳሳይ ፆታ “ያልተለመዱ” ጥንዶችን በአንዳንድ ሁኔታዎች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቅጃለሁ ሲሉ ተሰምተዋል።
ቫቲካን ይህንን ተከትሎ በሰጠው ማብራሪያ ይህ የሚሆነው በተለምዶ በቤተክርስትያኗ በሚካሄዱ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ እንዳልሆነ እና አሁንም ቢሆን ትዳር በአንድ ወንድና ሴት መካከል የሚደረግ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ ነው የምናየው ብሏል።
ይህንን ተከትሎም አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ሕብረት (ሴካም) በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ የሊቃ ጳጳሱን አዋጅመም ውድቅ ማድረጉነብ አስታውቋል።
የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤዎች ሕብረት ሴካም) በመወከል በኮንጎ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ተፈርሞ የወጣው መግለጫው፤ በተመሳሳይ ጾታ የሚፈጸም ህብረት “ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የሚቃረን” ነው ብሏል።
ተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በተመለከተ ከቫካን የወጣው አዋጅ የአፍሪካውያን ብል እና እሴትን የሚጥስ እንደሆነም የአፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ህብረት አስታውቋል።
ሴካም ከጋና ዋና ከተማ አክራ በሰጠው መግለጫ “በክርስቲያናዊ ጋብቻ እና ግንኙነት ላይ ያለው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አልተለወጠም” ብሏል።
"በዚህም ምክንያት የአፍሪካ ጳጳሳት በአፍሪካ የተመሳሳይ ጾታ ጥንዶችን መባረክ ተገቢ ነው ብለን አንወስደውም" ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።
የተመሳሳይ ጾታ ጥምረት ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴትን የሚጥስ በመሆኑ ተቀባይነት እንደማይኖረመው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሳሰቧ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፤ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንደማትባርክ መግለጿ ይታወሳል።
“ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በየትኛውም መልክ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን አትፈቅድም፤ አታጸድቅም” ያለው መግለጫው ጋብቻ ማለት በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ ህብረት መሆኑን አስረድቷል።
የሮማ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቃድ ሰጡ የሚለው መረጃ መሰማቱን ተከትሎ የተለያዩ ድጋፎችና ተቃውሞዎችን አስተናግዷል።
የዩክሬን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቫቲካን የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠትን አስመልክቶ ያወጣውን ውሳኔ እንደማትቀበል አስተውቃለች።
በተቃራኒው ከቫቲካን የተሰማው ዜና በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ዘንድ ትልቅ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል።