የሮማው ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎን ሊጎበኙ ነው
አባ ፍራንሲስ በሚቀጥለው ሳምንት የሚያደርጉት ጉብኝት አለም ለኮንጎ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግን ያለመ ነው ተብሏል
ኮንጎ 45 ሚሊዮን የሚጠጉ የካቶሊክ አማኞች የሚኖሩባት ሀገር ናት
የሮማው ጳጳስ አባ ፍራንሲስ በአፍሪካ ትልቁ የካቶሊክ ማህበረሰብ ያላትን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎን ለመጎብኘት አቅደዋል።
በኮንጎ የቫቲካን አምባሳደር ሊቀ ጳጳስ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ እንዳሉት አባ ፍራንሲስ በሚቀጥለው ሳምንት ኮንጎን የሚጎበኙ ይሆናል፡፡
45 ሚሊዮን የሚጠጉ ካቶሊኮች የሚኖሩባት ኮንጎ፣ ከ1985 ዓ.ም ወዲህ የመጀመሪያውና ታሪካዊ ነው የተባለለትን የካቶሊክ ቤተክርስትያን መሪ ጉብኝት ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ነች ተብሏል።
የአባ ፍራንሲስ የኮንጎ ጉብኝት ከአስርተ ዓመታት በፊት በማዕድን በበለጸገችው የአፍሪካ ሀገር የተቀሰቀሰውንና የሚሊዮኖች ህይወት የቀጠፈውን አሳዛኝ ክስተት ዓለም ችላ እንዳይለው ለማሳሰብ ያለመ እንደሆነም ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ ገልጸዋል።
አክለውም “ አሁን አባ ፍራንሲስን የምትቀበል ኮንጎ ከ38 ዓመታት በፊት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን የተቀበለችው ሀገር አይደለችም” ብለዋል።
ኮንጎ አሁንም ድረስ የተለያዩ ግጭቶች የሚስተዋሉባት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡
ባለፈው ሳምንት በምስራቅ ኮንጎ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 5 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡
በተለይም በኮንጎ መንግስት ኃይሎች እና "ኤም-23" አማጺ ቡድን መካከል ሲደረግ የቆየው ውጊያ የበርካታ ንጹሃን ህይወት የቀጠፈ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡