ፖፕ ፍራንሲስ በአየር ንብረት ለተጎዱ ደሃ ሀገራት የእዳ ስረዛ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
ፖፕ ፍራንሲስ ለኮፕ 28 ጉባዔ ለተሰባሰቡ የዓለም ሀገራት መሪዎች ጥሪ አስተላልፈዋል
የሮማው ሊቀጳጳስ “አካባቢን ማውደም እግዚአብሄርን እንደመስደብ ነው ብለዋል”
የሮማ ካቶሊክ ሊቀጳጳስ ፖስ ፍራንሲስ በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ደሃ ሀገራት የእዳ ስረዛ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ በተወካያቸው በኩል በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው 28ኛው የተመድ የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ28) ላይ ለዓለም ሀገራት መሪዎች ጥሪ አስተላልፈዋል።
- ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጮችን መደገፍ እንደሚገባ የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
ፖፕ ፍራንሲስ በቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኩል ባስተላለፉት መልእክትም፤ “አካባቢን ማውደም እግዚአብሄርን እንደመስደብ ነው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ከጎናችሁ ነኝ” ብለዋል።
የዓለም መሪዎች የአለም ሙቀት መጨመርን በመጋፈጥ አስገዳጅ ሁኔታ ላይ እንዲደርሱ ያሳሰቡት ፖፕ ፍራሲስ፤ በጋራ ለውጥ የምናስመዘግብበት አዲስ መንገድ ያስፈልጋል ሲሉም አብራርተዋል።
የሮማ ካቶሊክ ሊቀጳጳስ ፖስ ፍራንሲስ አክለውም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ለደረሰባቸው ደሃ ሀገራት የእዳ ስረዛ ሊደረግ ይገባል ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የሮማ ካቶሊክ ሊቀጳጳስ ፖስ ፍራንሲስ ከቀድመ ብለው በኮፕ28 ላይ እንደሚሳተፉ አሳውቀው የነበረ ቢሆንም፤ በጤና እክል ምክንያት በጉባዔው ላይ መሳተፍ አልቻሉም።
በትናትናው እለት በመሪዎች ደረጃ የተጀመረው የአየር ንብረት ለውጥ የተግባር ጉባዔ ዛሬ ቅዳሜ እለት ሁለተኛው ቀኑን የያዘ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ንግግር በማድረግ ላይ ይገኛሉ።