የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንደማትባርክ ገለጸች
የሮማ ሊቀ ጳጳስ የቤተ ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ መፍቀዳቸው ይታወሳል
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ መግለጫ አዉጥቷል
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን እንደማትፈቀድና ቡራኬም እንደማትሰጥ አስታወቀች።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ባሳለፍነው ሰኞ የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቃድ መስጠታቸው ይታወሳል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ አዲሱን የቫቲካን መመሪያ የሚያትቱ መዛግብትን ማፀድቃቸውን ተከትሎ ነበር የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቃድ መስጠታቸው የተሰማው።
ፖፕ ፍራንሲስ፤ የቤተ-ክርስትያኒቱ ቄሶች የተመሳሳይ ፆታ “ያልተለመዱ” ጥንዶችን በአንዳንድ ሁኔታዎች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቅጃለሁ ሲሉ ተሰምተዋል።
ቫቲካን ይህንን ተከትሎ በሰጠው ማብራሪያ ይህ የሚሆነው በተለምዶ በቤተክርስትያኗ በሚካሄዱ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ እንዳልሆነ እና አሁንም ቢሆን ትዳር በአንድ ወንድና ሴት መካከል የሚደረግ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ ነው የምናየው ብሏል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፤ የሊቀ ጳጳሱ መልዕክት በተቃራኒው ተወስዷል ብሏል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በአዲሱ የቫቲካን መመሪያ ሰነድ ላይ መወያየቱን እና ሰነዱ የቤተክርስቲያኒቱ ሚስጢር የሆነውን የጋብቻ ህብረት በአንዲት ሴትና በአንድ ወንድ መካከል የሚፈጸም መሆኑ ላይ ምንም አይነት ቀኖናዊ ለውጥ የማያመጣ መሆኑን አስታውቋል።
በመሆኑም ሰነዱ ለተሳሳይ ጾታ ጥምረት እውቅና ስለመስጠትና በሚስጢረ ተክሊል ደረጃ ባልና ሚስት ተድርጎ ስለመባረክ ፍቃድ የመስጠት ሀሳብ እንደሌለውም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አብራርታለች።
“ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በየትኛውም መልክ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን አትፈቅድም፤ አታጸድቅም” ያለው መግለጫው ጋብቻ ማለት በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ ህብረት መሆኑን አስረድቷል።
“ቤተ ክርስቲያን ኃጥያትን አትባርክም ታወግዛለች እንጂ” ያለው መግለጫው፤ ቀኖናዊ ከሆነው የአንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ጋብቻ ውጪ ያሉ ማንኛውም ጾታዊ ግንኙነቶችን እንደማትባርክም አረጋግጧል።
የተመሳሳይ ጾታ ጥምረት ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴትን የሚጥስ በመሆኑ ተቀባይነት እንደማይኖረመውም አሳስባለች።
የሮማ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠት እንዲችሉ ፈቃድ ሰጡ የሚለው መረጃ መሰማቱን ተከትሎ የተለያዩ ድጋፎችና ተቃውሞዎችን አስተናግዷል።
የዩክሬን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቫቲካን የቤተ-ክርስትያኗ ካህናት ለተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች ቡራኬ መስጠትን አስመልክቶ ያወጣውን ውሳኔ እንደማትቀበል አስተውቃለች።
በተቃራኒው ከቫቲካን የተሰማው ዜና በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ዘንድ ትልቅ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል።