በ5 ቢሊየን ዶላር አዲስ ዋና ከተማ ማስገንባት የጀመረችው ምስራቅ አፍሪካዊት ሀገር
ታንዛኒያ በቀድሞው ፕሬዝዳንቷ ጆን ማጉፉሊ የሚሰየም አዲስ ዋና ከተማ በመገንባት ላይ ትገኛለች
የአስተዳደር ቢሮዎች መቀመጫ የሚሆነው አዲስ ዋና ከተማ በ617 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል ተብሏል
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ታንዛኒያ በ5 ቢሊየን ዶላር አዲስ ዋና ከተማ እያስገነባች መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በ2021 በስልጣን ላይ እያሉ ህይወታቸው ባለፈው የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ስም ይሰየማል የተባለው አዲስ ዋና ከተማ የዲፕሎማቲክ እና የአስተዳደር ቢሮዎች መቀመጫ እንደሚሆን ተገልጿል።
617 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው አዲሱ ከተማ ከአሁኗ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ዶዶማ በ17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚንስቴር መስርያ ቤቶች እና የአስተዳደር ቢሮዎች ግንባታ የተጀመረ ሲሆን ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በዋና ከተማዋ የሚገኙ የፕሬዝዳንቷን ቢሮ ጨምሮ ሌሎች የአስተዳደር ቢሮዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ አዲሱ ከተማ እንደሚዘዋወሩ ተሰምቷል፡፡
የታንዛኒያ መንግስት የአስተዳደር ቢሮዎችን በአንድ ስፍራ መሰብሰብ የቢሮክራሲ አሰራሮችን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል ብሏል፡፡
የሀገሪቱ የቤቶች ኮርፖሬሽን ከተማውን በዋናነት በሃላፉነት ተቀብሎ እያስገነባ የሚገኝ ተቋም ነው።
የአፍሪካ ሀገራት አዳዲስ የአስተደደር እና የመኖሪያ ከተሞች ግንባታን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው፡፡
ግብጽ ከዋና ከተማዋ ካይሮ 48 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በአይነቱ ግዙፍ እና ዘመናዊ የሆነ የአስተዳዳር ከተማ ግንባታ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡
በአሁኑ ወቅትም 1500 የሚጠጉ ግብጻውያን ወደ አዲሱ ከተማ መዘዋወራቸው የተነገረ ሲሆን በ2024 መጨረሻም 10 ሺህ ሰዎችን ወደ ከተማው ለማዘዋወር እቅድ ተይዟል፡፡
ከዚህ ባለፈም በተጠናቀቁ የአስተዳደር ህንጻዎች ላይ 48 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች በአዲሱ ከተማ ስራ ጀምረዋል፡፡
ኒውስ ዊክ በዘገባው በአፍሪካ ግንባታቸው የተጀመረ ወይም ለመገንባት የታቀዱ ሜጋ ፕሮጄክት ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ ኤርፖርት ግንባታን ጠቅሶታል፡፡
በአህጉሪቷ በግዝፈቱ ቀዳሚው ይሆናል የተባለው አውሮፕላን ማረፊያ በአመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ሲኖረው እስከ 2029 ግንባታው እንደሚጠናቀቅም ገልጿል፡፡
በሴኔጋል በ6 ቢሊየን ዶላር ለመገንባት የታቀደው አዲስ ከተማም ከነዚህ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡