በ30 አመታት ውስጥ በማርስ ሰዎች የሚኖሩበት ከተማ እንገነባለን - መስክ
በቀጣይ አስር አመታት ሰዎችን ማርስ ላይ ማስፈር እንደሚጀመርም የስፔስኤክስ መስራቹ ኤለን መስክ ተናግረዋል
በፈረንጆቹ 2002 የተመሰረተው ስፔስኤክስ ወደአለማቀፉ የህዋ ጣቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ መንኮራኩር የላከ የግል ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል
ማርስ ላይ በቀጣይ 30 አመታት ውስጥ ግዙፍ የሰዎች መኖሪያ ከተማ እንገነባለን አሉ ቢሊየነሩ ኤለን መስክ።
የስፔስኤክስ ኩባንያ መስራቹ መስክ ከአምስት አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሰዎች ያልተሳፈሩባቸው መንኮራኩሮችን ወደ ማርስ መላክ እንጀምራለን ብለዋል።
በ10 አመታት ውስጥም ሰዎችን ማርስ ላይ ማስፈር እንደሚጀመርና በ30 አመት ውስጥ ማርስ የሰው ልጆች የሚኖሩበት የሰለጠነ ከተማ እንገነባለን ሲሉም በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በ44 ቢሊየን ዶላር በገዙት ኤክስ (ትዊተር) 183 ሚሊየን ተከታዮች ያላቸው መስክ ዜናውን ማጋራታቸውን ተከትሎ በርካቶች ተስፋና ስጋታቸውን አጋርተዋል።
በፈረንጆቹ 2002 የተመሰረተው ስፔስኤክስ ወደ አለማቀፉ የህዋ ጣቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ መንኮራኩር እና ጠፈርተኞችን የላከ የግል ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል።
የማርስ የከተማ ግንባታውን እውን ለማድረግ ስፔስኤክስ በርካታ የቅኝት ሳተላይቶችን እንደሚልክ አስታውቋል።
ቢሊየነሩ መስክ ለህዋ ምርምር የተለየ ፍቅር እንዳላቸው ይነገራል።
በ2024 መጀመሪያም ወደ ህዋ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተደረገባት ግዙፍ ሮኬት ማስወንጨፋቸው ይታወሳል።
120 ሜትር የሚረዝመው “ስታርሺፕ” ሮኬት ሰዎችን እና ሳተላይቶችን ወደ ጨረቃና ማርስ በፍጥነት ለማምጠቅ ያስችላል መባሉም አይዘነጋም።