የስዊድኗ ጎተን ከተማ አዲስ ነዋሪዎችን ለመሳብ የቤት መስሪያ መሬት በ10 ሳንቲም አቀረበች
5 ሺህ ነዋሪ ያለባት ከተማዋ የአዛውንቶች እና ህጻናት የማይወለድባት ከተማ ሆናለች
ከተማዋ ማንኛውም ሰው መጥቶ መሬት በርካሽ እንዲገዛ እና መኖሪያ ቤት እንዲገነባ የሚያበረታታ ህግ አውጥታለች
በነዋሪዎች ድርቅ የተመታችው የስዊድኗ ጎተን ከተማ ቤት መስሪያ መሬት በርካሽ አቀረበች፡፡
የስዊድኗ ጎተን ከተማ በአውሮፓ ካሉ ከተሞች መካከል በየዓመቱ አነስተኛ ህጻናት ከሚወለዱባቸው ከተሞች መካከል አንዷናት፡፡
እንዲሁም ይህች ከተማ በእድሜ የገፉ ሰዎች ከሚኖሩባት ከተሞች መካከልም አንዷ ስትሆን የከተማዋ አስተዳድር ተጨማሪ ነዋሪዎች እንዲመጡ ማበረታቻዎችን ዘርግቷል፡፡
ለሁለት ዓመት ይቆያል የተባለው ይህ ማበረታቻ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ በጎተን ከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በርካሽ አቅርቧል፡፡
የከተማዋ ከንቲባ ጆሃን ማንሰን ለዩሮ ኒውስ እንዳሉት ወደ ጎተን ከተማ መጥተው ለሚኖሩ እና ቤት መስራ ለሚፈልጉ ሰዎች አንድ ስኩዌር ሜትር ቦታ በአንድ የስዊድን ክሮና ወይም በ0 ነጥብ 08 ዶላር ዋጋ እንሸጣለን ብለዋል፡፡
ይህ ማበረታቻ ከተያዘው 2024 ጀምሮ እስከ ቀጣዩ ዓመት ድረስ ይቆያል ያሉት ከንቲባው ለሽያጭ የቀረበው ቦታ ለመኖሪያ ምቹ በሆኑ በከተማዋ እምብርት ላይ የሚገኝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
“ለማንኛውም ሰው መሬቱን ለመሸጥ ዝግጁ ነው ዋናው እዚህ እኛ ከተማ መጥቶ ለመኖር ፍላጎት ብቻ ይኑረው” ሲሉም ከንቲባው አክለዋል፡፡
ይሁንና መሬቱን የገዙ ነዋሪዎች በሁለት ዓመት ውስጥ መኖሪያ ቤቱን መገንባት አልያም ግንባታውን መጀመር እንደሚኖርባቸው ይህ ካልሆነ ግን መሬቱን ሊነጠቁ እንደሚችሉ በዘገባው ላይተጠቅሷል፡፡
ጎተን ከተማ በአውሮፓ ካሉ ውብ ስፍራዎች መካከል አንዷ ስትሆን በመልክዓ ምድር አቀማመጥ፣ የዱር እንስሳት እና ሌሎች የሚጎበኙ ስፍራዎችን የያዘች ከተማ ናት፡፡
ከተማዋ ማስታወቂያውን ካወጣች በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ሶስት የመኖሪያ ቤት መሬት የተሸጠ ሲሆን በቀጣዮቹ ጊዜያት ተጨማሪ ገዢዎች እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡