ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የአፍሪካ ሀገራት ምን አሉ?
ኢራን በእስራኤል ላይ ከ300 በላይ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን ተጠቅማ ጥቃት ሰንዝራለች
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሁለቱ ሀገራት ውጥረትን ከሚያባብሱ ተግባራት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል
ኢራን ቅዳሜ ሌሊት ለመጀመሪያ ጊዜ በፈተጸችው ቀጥተኛ ጥቃት ወደ እስራኤል በርካታ ቁጥር ያላቸው ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን መተኮሷን አስታውቃለች።
በጥቃቱም ኢራን ወደ አስራኤል ከ300 በላይ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን የተኮሰች ሲሆን፤ እስራኤል ከተተኮሰባት ውስጥ 99 በመቶውን ማክሸፏን አስታውቃለች።
ይሁን እንጂ የእስራኤልን የአየር መከላከያ ጥሰው የገቡ ድሮኖችና ሚሳዔሎች ጉዳት ማድረሳቸውን የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታውቋል።
በዚህም የ7 ዓመት ህጻን ልጅን ጨምሮ 12 ሰዎች ቆስለዋል የተባለ ሲሆን፤ በደቡብ እስራኤል የሚገኝ የአየር ኃይል ማዘዣ ላይም መጠነኛ ጉዳት ደርሷል።
ጥቃቱን ተከትሎም በርካታ የአፍሪካ እና የዓለም ሀገራት በሰሞነኛው ጥቃትና በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ዙሪያ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
የእስራኤል ጦር ካቢኔ ለኢራን በሚሰጠው ምላሽ ዙሪያ መወያየቱን ተከትሎ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እስራኤል ውጥረትን እና ግጭትን ከሚያባብሱ ተግበራት እንድትቆጠብ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ኢራን እና እስራኤል ግጭትን ከሚያባብሱ ተጨማሪ ተግባራት እንዲታቀቡ ካሳሰቡ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫው፤ ሁሉም ወገኖች በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ተጨማሪ ግጭትን ከሚቀሰቀሱ ተግባራት በከፍተኛ ሁኔታ ራሳቸውን እንዲያቅቡ ጥሪ አቅርቧል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ “ሁሉም ወገኖች ግጭቱ የሚያስከትለውን ከባድ አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ራሳቸውን ከግጭት እንዲቆጥቡ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ አክለውም ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችው ጥቃት "በአለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት ላይ የተደቀነውን ወቅታዊ ስጋትን ይወክላል" ብለዋል።
ሶማሊያ በበኩሏ ባወጣችው መግለጫ “የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁኔታውን ለማርገብ እና በቀጣይ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል አፋጣኝ እና ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ” ጠይቃለች።
የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል እና ኢራን "ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኝነታቸውን እንዲያንጸባርቁ" አሳስቧል።
ኢራን በእስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ እና ቀጥተኛ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትም መግለጫ ያወጡ ሲሆን፤ ተመድም ለሁለቱ ወገኖች ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
የተባባሩት ምግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኢራንን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፤ ሁሉም አካላት ራሳቸውን ከግጭት እንዲቆጥቡ አሳስበዋል።
ጉቴሬዝ አክለውም፤ መካከለኛው ምስራቅ ቀጠናም ይሁን ዓለም አሁን ላይ ተጨማሪ ጦርነት መቋቋም አይችልም ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ “አሜሪካ በእስራኤል ላይ ያላት ፖሊሲ እንደ ብረት የጠነከረ ነው” ያሉ ሲሆን፤ የብሪታያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ እና የጀርመኑ መራሄ መንግስት ስቾልዝ የባይደንንን ሀሳብ ደግፈው መግለጫ ሰጥተዋል።