አሜሪካ “እስራኤል በኢራን ላይ በምትወስደው የአጻፋ እርምጃ እጄን አላስገባም” አለች
ኢራን በበኩሏ አሜሪካ የእስራኤልን መልሶ ማጥቃት የምታግዝ ከሆነ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎቿን እመታለሁ ስትል ዝታለች
የእስራኤል የጦር ካቢኔ በኢራን ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ተስማምቷል
አሜሪካ “እስራኤል በኢራን ላይ በምትወስደው የአጻፋ እርምጃ እጄን አላስገባም” አለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ ሲወያዩ እስራኤል የምትወስደው የአጻፋ እርምጃ “ጥንቃቄ የበዛበት” እንዲሆን ማሳሰባቸው ተገልጿል።
ባይደን ከኢራን ከተተኮሱ ከ300 በላይ ሚሳኤሎች እና ድሮኖች ማክሸፍ የቻለችው እስራኤል ወታደራዊ የበላይነቷን ያሳየችበት መሆኑን ለኔታንያሁ መናገራቸውን የጠቀሰው ሬውተርስ፥ ቴል አቪቭ ምላሽ እንዳትሰጥ ስለማስጠንቀቃቸው ግን ያለው ነገር የለም።
የአሜሪካ የጦር መርከቦች እና አውሮፕላኖች ከኢራን የተተኮሱ ከ80 በላይ ድሮኖች እና ስድስት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን በኢራቅ ሰማይ መተው መጣላቸው ተመላክቷል።
ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተጨማሪ ጦር የላከችውና የጦር መርከቦቿን ከኢራን የሚተኮሱ ሚሳኤሎችን እንዲያከሽፉ ዝግጁ ያደረገችው ዋሽንግተን፥ ቴል አቪቭ ለምትፈጽመው የአጻፋ ምላሽ ግን ድጋፍ አላደርግም ብላለች።
የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባዩ ጆን ኪርቢ፥ እስራኤል በኢራን ላይ ከምትፈጽመው ጥቃት ውጭ ግን የዋሽንግተን ወታደራዊ ድጋፍ እንደማይለያት ነው ያነሱት።
አምስት አባላት ያሉት የእስራኤል የጦር ካቢኔ በትናንትናው እለት ባካሄደው ስብሰባ በኢራን ላይ በሚፈጸመው የአጻፋ እርምጃ ላይ ቢስማማም መቼ እና በምን ያህል መጠን በሚለው ዙሪያ ልዩነቶች ተንጸባርቀዋል ተብሏል።
የጦር ካቢኔው አባል ቤኒ ጋንዝ “ቀጠናዊ ጥምረት መስርተን እኛ በሚመቸን ጊዜ እና ሁኔታ በኢራን ላይ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንትም ኢራን የፈጸመችው ጥቃት እስራኤል ስትራቴጂካዊ አጋሮችን እንድታፈራ እንደሚያደርጋትና አጻፍዊ እርምጃው አይቀሬ ስለመሆኑ የሚያመላክት አስተያየት ሰጥተዋል።
ኢራን በበኩሏ እስራኤል የአጻፋ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ ቀጣዩ ጥቃት ይከፋል ስትል አስጠንቅቃለች።
አሜሪካም የእስራኤልን መልሶ ማጥቃት የምታግዝ ከሆነ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎቿ እንደሚመቱ ነው የኢራን ጦር አዛዥ ሜጄር ጀነራል ሞሀመድ ባግሃሪ ያሳሰቡት።