ጆርዳን፣ ኢራቅና ሊባኖስን ጨምሮ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የአየር ክልላቸውን እየዘጉ ነው
ኢራን ወደ እስራኤል በርካታ ቁጥር ያላቸው ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን መተኮሷን አስታወቀች
እስራኤል ባሳለፍነው ሳምንት በሶሪያ መዲና ደማስቆ በሚገኝ የኢራን ኢምባሲ ላይ ባደረሰችው ጥቃት ሁለት ወታደራዊ አዛዦችን ጨምሮ ዘጠኝ ኢራናዊያ መገደላቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ በኢምባሲዋ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስራኤልን እንደምትበቀል ስትዝት የቆየችው ኢራን በዛሬው እለት መጠነ ሰፊ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃተ ወደ ቴልአቪቭ መክፈቷን አስታውቃለች።
የኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ ዛሬ ምሽት በሰጠው መግለጫው፤ ወደ እስራኤል ድንበር በርካታ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን መተኮሱን አስታውቋል።
እስራኤል እንደስታወቀችው ከ300 በላይ ድሮኖች አና ሚሳዔሎች ከኢራን፣ የመን እና ኢራቅ ውስጥ ወደ እስራኤል ተተኩሰዋል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ አድሚራል ዳንኤል ሀግሪ፤ ወደ እስራኤል ከተተኮሱ ከ300 በላይ ድሮኖና ሚሳኤሎች ውስጥ 99 በመቶውን ማክሸፍ እንደተቻለ ተናግረዋል።
በአሜሪካ እና በብሪታኒያ እርዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢራን ድሮኖችና ሚዔሎች ድንበር ላይ ተመትተው ወድቀዋል።
ኢራን ካህይበር የተባለው አደገኛው ሚሳዔል ወሳኝ የሆነ የእስራኤል የአየር ኃይል ጣቢያን መምታቱን የኢራን ዜና አገልግሎት አስታውቋል።
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የፈጸመችው በሶሪያ ደማስቆ በሚገኘው ኢምባሲዋ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስራኤልን ለመበቀል ነው።
የአየር ክልሎች መዘጋት
ኢራን ወደ እስራኤል ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን እንደተኮሰች ማሳወቋን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ሁኔታ በፍጥነት እየተቀያየረ ሲሆን፤ መንግስታትም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛል።
ጆርዳን፣ ሊባኖስ እና ኢራቅ የአየር ክልላቸውን መዝጋታቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ እነዚህ ሶስቱ ሀገራት የኢራን ድሮኖች እና ሚሳዔሎች ሊያልፉባቸው የሚችሉ ናቸው ተብሏል።
ኢራን እና እስራኤልም ከወታደራዊ አውሮፕላኖች በስተቀር ለሌሎች አውሮፕላኖች የአየር ክልላቸውን መዝጋታቸው ነው እየተነገረ ያለው።
አሜሪካ ስለ ጥቃቱ ምን አለች?
ኢራን በእስራኤል ላይ የአየር ወለድ ጥቃትን መጀመሯን የአሜሪካው ነጩ ቤተ መንግስት ወይም ዋይት ሀውስ አስታውቋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በብሔራዊ ደህንነት ቡድናቸው አማካኝነት ስለሁኔታው በመደበኛነት እየተከታተሉ መሆኑም ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ቡድናቸው ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር በተደጋጋሚ ግንኙነቶችን እያደረጉ እየተወያዩ መሆኑን ዋይት ሃውስ አስታውቋል።
አሜሪካ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተጨማሪ ኃይል መላኳም ይታወሳል።
ዋሽንግተን ተጨማሪ ኃይል የላከችው ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል ጥቃት ትፈጽማለች የሚለው ስጋት ባየለበት ወቅት ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢራን በሶሪያ ለተገደሉባት ጀነራሎች ተጠያቂ ባደረገቻት እስራኤል ላይ እፈጽመዋለሁ ካለችው የአጻፋ እርምጃ እንድትቆጠብ ማሳሰባቸውም ይታወሳል።
እስራኤልም ኢራን ልትቃጣው የምትችለውን ማንኛውም አይነት ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ መሆኗን ስትገልጽ ቆይታለች።