ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ሀገራት ምን አሉ?
አረብ ኢምሬትስ፣ ሩሲያ፣ ቻይናና ዩክሬንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት መግለጫ አውጥተዋል
የተመድ ዋና ጸሃፊ “ዓለም ሌላ ተጨማሪ ጦርነት ማስተናገድ አትችልም” ብለዋል
ኢራን ሌሊቱን ለመጀመሪያ ጊዜ በፈተጸችው ቀጥተኛ ጥቃት ወደ እስራኤል በርካታ ቁጥር ያላቸው ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን መተኮሷን አስታውቃለች።
በጥቃቱም ኢራን ወደ አስራኤል ከ300 በላይ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን የተኮሰች ሲሆን፤ እስራኤል ከተተኮሰባት ውስጥ 99 በመቶውን ማክሸፏን አስታውቃለች።
ይሁን እንጂ የእስራኤልን የአየር መከላከያ ጥሰው የገቡ ድሮኖችና ሚሳዔሎች መጠነኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታውቋል።
በዚህም የ7 ዓመት ህጻን ልጅን ጨምሮ 12 ሰዎች ቆስለዋል የተባለ ሲሆን፤ በደቡብ እስራኤል የሚገኝ የአየር ኃይል ማዘዣ ላይም መጠነኛ ጉዳት ደርሷል።
ጥቃቱን ተከትሎም የዓለም ሀገራት አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
አረብ ኢምሬትስ
የአረብ ኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ፤ ሁሉም ወገኖች ከጠናውን ወደ ግጭት ከሚያስገቡ ነገሮች እንዲቆጠቡ አሳስስቧለረ።
የኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አለመግባባቶች በውይይት እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ፣ የህግ የበላይነትን እንዲያከብር እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተርን እንዲከበር ጥሪ አቅርቧል።
ቻይና
ቻይና ከኢራን ጥቃት በኋላ የሁኔታዎች መባባስ በጣም እንዳሳሰባት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይጽህፈት ቤት በድረ-ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቀዋል።
ቻይና ተጨማሪ ውጥረቶችን ለማስቀረት የሚመለከታቸው አካላት እንዲረጋጉ እና ራሳቸውን ወደ ግጭት ከሚያስገቡ ተግባራት እንዲቆጥቡም ጠይቃለች።
የአሁኑ ውጥረት የጋዛ ግጭት ግጭት መዘዝ ነው ያለችው ቻይና፤ ችግሩን ለመቅረፈ የጋዛውን ግጭት ማቆም ቅድሚያ የሚሰጠው መሆን ንዳለበትም አሳስባለች።
ግብጽ
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫው፤ በቀጠናው ያለው ውጥረት መባባሱ እንዳሳሰበው በመግለጽ፤ ሁሉም ወገኖች ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ ግጭትን ከሚያባብሱ ተግባራት እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ግጭቱ ሊስፋፋ እንደሚችል ስጋቱን ያስቀመጠው መግለጫው፤ ግብጽ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ግጭቱ ውስጥ ካሉ ሁሉም አካላት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደምታደርግም አስታውቋል።
ሩሲያ
ሩሲያ ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችው ጥቃት ክፉኛ እንዳሳሰባት በመግለጽ፤ ሁሉም አካላት ግጭትን ከሚያባብሱ ተግባራት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቀርባለች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ “በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና እየተባባሰ የመጣው ሁኔታ በጣም አሳስቦኛል፤ ሁሉም ሀገራት ራሳቸውን ከግጭት እንዲያርቁ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል።
ሳዑዲ አረቢያ
የሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የወታደራዊ ፍጥጫዎች መባባስ ስጋት እንደፈጠረ በመግለጽ “ሁሉም አካላት ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ ግጭት ከሚያባብስ ሁኔታ እንዲቆጠቡ እና ክልሉን እና ህዝቦቹን ከጦርነት አደጋ እንዲታደጉ” ጥሪ አቅርቧል።
ዩክሬን
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የኢራንን ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የሚሳኤል ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፤ በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት እንዳይባባስ ጥረቶችን እንዲደረጉ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት
የተባባሩት ምግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኢራንን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፤ ሁሉም አካላት ራሳቸውን ከግጭት እንዲቆጥቡ አሳስበዋል።
ጉቴሬዝ አክለውም፤ መካከለኛው ምስራቅ ቀጠናም ይሁን ዓለም አሁን ላይ ተጨማሪ ጦርነት መቋቋም አይችልም ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ “አሜሪካ በእስራኤል ላይ ያላት ፖሊሲ እንደ ብረት የጠነከረ ነው” ያሉ ሲሆን፤ የብሪታያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ እና የጀርመኑ መራሄ መንግስት ስቾልዝ የባይደንንን ሀሳብ ደግፈው መግለጫ ሰጥተዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ሀገራቸው ከኢራን የሚሰነዘርባትን ማንኛውም ጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅ እንደምትገኝ ገልጸው፤ “እኛን የጎዳ ሁሉ ይጎዳል” ሲሉ ዝተዋል።
የኢራኑ መሪ አያቶላህ አሊ ከህሚኒ በሰጡት አስተያየት “ጺዮናዊው አስተዳደር ይቀጣል” ሲሉ የዛቱ ሲሆን፤ በተመድ የኢራን ተወካይ በበኩላቸው አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባ አስተንቅቀዋል።