በሰሜን ሶማሊያ የአይኤስ ታጣቂዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ ተነገረ
በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ዕዝ (አፍሪኮም) ቡድኑ ከሌሎች አገራት የመለመላቸውን አባላቱን በሶማሊያ እያከማቸው ይገኛል ብሏል
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር የሽብር መከላከል ስራውን እንደጎዳው ተነግሯል
በሰሜናዊ ሶማሊያ የእስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ታጣቂዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ዕዝ (አፍሪኮም) አስታወቀ፡፡
በስፍራው የታጣቂዎች ቁጥር በሁለት እጥፍ ማደጉን የተናገሩት የዕዙ ዋና አዛዥ ማይክል ላንግሊ ቡድኑ በአካባቢው አዳዲስ ታጣቂዎችን እየመለመለት ሲሆን በተጨማሪም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ አባላቱን በስፍራው እያከማቸ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አዛዡ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአሁኑ ወቅት በስፍራው የሚገኙ የአይኤስ ታጣቂዎች ቁጥር ስንት እንደሆነ ይፋ ባያደርጉም ባለፈው አመት በወጡ መረጃዎች እስከ 200 የሚደርሱ የቡድኑ አባላት እንደሚገኙ ተነግሮ ነበር፡፡
በዚህም በአንድ አመት ውስጥ በሁለት እጥፍ አድገዋል ከተባለ እስከ 600 የሚደርሱ የቡድኑ አባላት በሰሜን ሶማሊያ እየተንቀሳቀሱ ሊሆን ይችላል ሲል የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል፡፡
በሶማሊያ የአይኤስ ቡድን መሪ ነው የተባለው አብዱልቃድር ሙሚን ባሳለፍነው ሰኔ አሜሪካ ከፈጸመችው የአየር ጥቃት መትረፍ መቻሉ ይታወሳል፡፡
የአፍሪኮም ዋና አዛዥ ማይክል ላንግሊ የአልሸባብ ወታደራዊ አቅም በሰው ሀይል እና ጦር መሳርያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከ12 – 13 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት የሚነገርለት አልሸባብ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እንደ ጥሩ አጋጣሚ እየተጠቀመበት እንደሚገኝ ነው ዋና አዛዡ የጠቀሱት፡፡
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ክፍተት የሽብር መከላከል ስራውን እንደጎዳው ገልጸው ሀገራቱ በጋራ በሰሩበት ወቅት የቡድኑን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማዳከም ችለው እንደነበረ አንስተዋል፡፡
ዋና ከተማዋን ሞቃዲሾን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረሱን የቀጠለው የሽብር ቡድን በቅርቡ በአጥፍቶ ጠፊ የቦንብ ፍንዳታ 32 ሰዎች ለሞቱበት ጥቃት ሃላፊነቱን ወስዷል፡፡
ከዚህ ባለፈም ባሳለፍነው ቅዳሜ በማዕከላዊ ሸበሌ ክልል እና በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግስት አንድ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሁለት የቦምብ ጥቃቶችን እድርሷል፡፡
በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል መንግስት በከፈተው ወታደራዊ ዘመቻ ተሸንፎ በርካታ ቦታዎችን ለቆ የነበረው አልሸባብ ማዕከላዊ ሶማሊያን ጨምሮ በሌሎች ስፍራዎች በመንግስት ጦር የተወሰዱበትን ስፍራዎች ድጋሚ እየተቆጣጠረ ነው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል አልሸባብ ከአልቃይዳ እና ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር ያለው ግንኙነት እየጨመረ እንደሚገኝ እና በሰሜናዊ ሶማሊያ ከኤደን ባህረሰላጤ ባሻገር ከሚገኘው የየመኑ ሁቲ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነ አፍሪኮም አስታውቋል፡፡
የሁቲ ታጣቂዎች ድሮን፣ ሚሳኤል እና ሮኬቶችን ለአል ሸባብ የማስታጠቅ ፍላጎት እንዳለቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም ምክንያት በአካባቢው የሚገኘው የሽብር እንቅስቃሴ ማደግ ለቀጠናው ሀገራት ፣ ለአለም አቀፍ ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እክል ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡