አልሸባብ ከሀውቲ ታጣቂዎች ጋር በትብብር እየሰራ ነው ተባለ
ሁለቱ ቡድኖች በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ የአሜሪካ እና የብሪታንያ መርከቦችን ለማጥቃት መስማማታቸው ተሰምቷል
በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የሀውቲ ታጣቂዎች ለአልሸባብ በቅርቡ ድሮኖችን ለመስጠት ቃል ገብተዋል
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው ሽብርተኛ ቡድን አል-ሸባብ ከየመን ሀውቲ ታጣቂዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የአሜሪካ የደህንንት ተቋማት ይፋ አድርገዋል፡፡
ሃውቲዎች ከአልሸባብ ጋር በፈጠሩት ህብረት በቀይ ባህር እና በህንድ ውቂያኖስ የሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ እና የብሪታንያ መርከቦችን በጋራ ለማጥቃት መስማማታቸውን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
ሀውቲዎች ከ2023 ጀምሮ በኤደን ባህረ ሰላጤ እና በቀይ ባህር 190 ጊዜ የአሜሪካ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ በህንድ ውቂያኖስ ላይ ያላቸውን ተጽእኖ ለማስፋት እቅድ ይዘዋል፡፡
በዚህ ስፍራ ከአልሸባብ ጋር በጋራ ለመስራት እቅድ ያወጡ ሲሆን ዘመናዊ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን ለአልሸባብ ለማስታጠቅ መስማማታቸውም ተሰምቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሃውቲዎች በደቡባዊ ሶማሊያ ቡድኑ በሚገኝበት ስፍራ የድሮን መቆጣጠርያ መሰረተ ልማቶችን የሚገነቡ ኢንጂነሮችን ልከዋል ነው የተባለው፡፡
አልሸባብ ባለፉት ሁለት አመታት በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ በተከፈተበት መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ለቋቸው የነበሩትን ስፍራዎች በሀውቲዎች ድጋፍ ድጋሚ በመቆጣጠር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ቡድኑ ባለፉት ሁለት አመታት በሶማሊያ መንግስት ብልጫ ተወስዶበት የለቀቃቸውን ስፍራዎች በአሁኑ ሰአት ሙሉ ለሙሉ ድጋሚ ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡
አሜሪካ ለአመታት ለአልሸባብ የሚደረገውን በሚሊየን ዶላር የሚቆጠር የጦር መሳርያ ድጋፍ እና ሽያጭ ለመቆጣጠር ብትሞክርም የተሳካ አይመስልም። በ2022 የሀገሪቱ ግምጃ ቤት ለአልሸባብ የጦር መሳርያ ያሳልፋሉ ባላቸው በስምንት ኩባንያ እና ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል፡፡
ባለፉት ሁለት አመታት የሶማሊያ ጦር በአልሸባብ ላይ በከፈተው መጠነ ሰፊ ዘመቻ የአልሸባብን ይዞታዎች ማጥበብ ችሎ ነበር። ሆኖም በወታደራዊ ስትራቴጂ ድክመት፣ ሙስና፣ ወታደራዊ አመራሮች ለጦሩ በሚላከው ምግብ እና ጥይት ስርቆት ላይ መሰማራታቸው ላይ አልሸባብ ከሀውቲ ያገኝው ድጋፍ ሲጨመር የተነጠቃቸውን ስፍራዎች በስድስት ወራት ማስመለስ አስችሎታል ነው የተባለው፡፡
የታጣቂዎች ቁጥር ቀንሶበት የነበረው ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ወደ ድሮ ይዞታው ተመልሶ ከ12-13ሺህ ታጣቂዎች እንዳሉት ይገመታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ ከጂቡቲ፣ ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የተውጣጣ ከ5 እስከ7ሺህ የሚገመት የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ይገኛል።
ከዚህ ውስጥ 3ሺህ የሚሆነው ወታደር የኢትዮጵያ ነው፡፡ ጥምር ጦሩ በአመቱ መጨረሻ በሶማሊያ ተልዕኮውን የሚያጠናቅቅ ሲሆን ሶማሊያ በበኩሏ ጦሩ ቆይታውን እንዲያራዝም በመጠየቅ ላይ ትገኛለች፡፡