የሶማሊያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ውጥረት በማባባስ ውስጣዊ የፖለቲካ ችግርን ለመሸፈን እየተጠቀመበት ነው- አምባሳደር ታዬ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አምባሳደር ታዬ ይህን ያሉት 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው
ሚንስትሩ ከአፍሪካ ቀንድ ውጭ ያሉ ኃይላት በቀጣናው ውጥረት ለመፍጠር ከሚያደርጉት ጥረት እንዲታቀቡ ጠይቀዋል
የሶማሊያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የሚገኝበትን ውጥረት በማባባስ የራሱን የውስጥ ፖለቲካ ችግር ለመሸፈን እየጣረ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ ተናገሩ፡፡
ሁለቱ ሀገራት አለመግባባት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ ሶማሊያ የሉአረዊ ግዛቷ አካል አድርጋ ከምታያት ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት በመፈራረሟ ምክንያት ነው።
ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ አለምአቀፍ ህግን እና ሉአላዊነቴን ጥሳለች የሚል ክስ በማቅረብ የኢትዮጵያ አምባሳደር እስከማባረር የደረሰ እርምጃ ወስዳለች።
አምባሳደሩ በመንግስታቱ ድርጅት 79ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የናይል ተፋሰስ ስምምነት ፣ የሶማሊያ እና የቀጠናው ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት በሶማሊያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ እና በቀጣናው የተሳሰረ እድገትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
መሰል ስምምነቶች በሌሎች አገራት ከአሁን በፊት የተፈረሙ መሆናቸውን አስታውሰው የሶማሊያ መንግሥት ውስጣዊ የፖለቲካ ችግሩን ለመሸፈን ካልሆነ በስተቀር ግጭት ቀስቃሽ ሥራዎችን እንዲሠራ የሚገፋፋ አንዳች የተለየ ነገር የለም ብለዋል።
ባለፈው አመት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የወደብ መግባብያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ በሞቃዲሾ እና አዲስ አበባ መካከል ቅራኔ ተፈጥሯል፡፡
ይህን ተከትሎም በቀጠናው በተለየ ፍጥነት እየቀረበች የምትገኝው ግብጽ ከሶማሊያ ጋር የተፈራረመችውን የመከላከያ ስምምነት መሰረት በማድረግ ለሶማሊያ በሁለት ዙር የጦር መሳርያ ድጋፎችን አድርጋለች፡፡
ይህን ተከትሎም በቀጠናው የሚገኝው ውጥረት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ክፍ ብሎ ታይቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በንግግራቸው የ120 ሚሊየን ህዝብ ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ ላይ ያለው የባህር ላይ ደህንነት ችግር ትልቅ ስጋት ነው ብለዋል።
በዚህ ቀጠና በሚገኝው የሰላም ሁኔታ ላይ የንግድ እንቅስቃሴዋ የሚወሰነው ኢትዮጵያ የአካባቢው ደህንነት ከማንኛውም አካል የበለጠ እንደሚያሳስባት ነው የገለጹት፡፡
ቀጠናው በግጭቶች፣ የባህር ላይ ወንበዴዎች እና ሌሎች ህገወጥ ተግባራት ስጋት ላይ ወድቋል ያሉት ሚንስትሩ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ የጸጥታ ችግሮችን በመዋጋት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቷን አስታውሰው በቀጣይ በባህሮች ላይ ሰላማዊ ጉዞን ለማረጋገጥ ከጎረቤቶቻችን ጋር በመሆን ጥረታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአሁኑ ወቅት በርካታ ፈተናዎች እያጋጠሙት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ችግሮችን ለመፍታት ወደ ቀደመ የባለብዙ ወገን ግንኙነት መርሆች መመለስ እንደሚገባ እና አባል አገራቱም በመካከላቸው ያለውን የትብብር መንፈስ በማጠናከር ለችግሮች የጋራ መፍትሄ ለማበጀት እንዲሰሩ ጥሪ አቅረበዋል፡፡
የጦር መሣሪያ እሽቅድድም፣አስከፊ ድህነት፣ኢ-ፍትሐዊነት፣የአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የገጠሙ መሠናክሎች የተመድ እና አባል አገራቱን ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ሚኒስትሩ በንግግራቸው አንስተዋል።