አሜሪካ፤ የአልሸባብ መሪን ለጠቆመኝ 5 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ አለች
አሊ ሙሐመድ ራጊ ከግንቦት 2009 ጀምሮ የአልሸባብ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለገለ የቡድኑ ቁልፍ ሰው ነው
ራጊ አልሻባብ በኬንያ እና ሶማሊያ የፈጸማቸውን የሽብር ጥቃቶች በማቀነባበር ወንጀል ይፈለጋል ተብላል
አሜሪካ፤ የአልሸባብ መሪን ለጠቆመኝ 5 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ አለች
አሜሩካ የአሸባሪው “አልሸባብ” መሪ አሊ ሙሐመድ ራጊ ያለበትን ስፍራ ለጠቆመ የ5 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት መድባለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የፍትህ ሽልማት ፕሮግራም ባወጣው መግለጫ፤ የገንዘብ ሽልማቱ የሚሰጠው የአሸባሪውን ቡድን መሪ ያለበትን ስፍራ በተመከለከተ መረጃ ለሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ነው፡፡
አሊ ሙሐመድ ራጊ፣ ከግንቦት 2009 ጀምሮ የአልሸባብ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለገለ የቡድኑ ቁልፍ ሰው ነው፡፡
የአሜሪካ መንግስት ሙሐመድ ራጊ፣ እጅግ በጣም ከሚፈለጉ አለም አቀፍ አሸባሪዎችን ዝርዝር ውስጥ ያስገባው እንደፈረንጆቹ በነሀሴ 2021 ነበር፡፡
የአሜሪካ መንግስት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ማናቸውም የአሊ ቴሪን ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ የሚል እግዳ መጣሉም አይዘነጋም፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም በተመሳሳይ እንደፈረምጆቹ የካቲት 18 ቀን 2022 በግለሰቡ ላይ ማዕቀብ ጥሏል፡፡
የተመድ የውሳኔ ሃሳቡ ሁሉም የተመድ አባል ሀገራት በአሊ ቲሪ ላይ የጦር መሳሪያ እና ስልጠና ማዕቀብ ፣ የገንዘብ ድጋፍ፣ ጉዞ እና የአሊ ሙሐመድ ራጊን ንብረቶችን ከማገድ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ጥብቅ ማዕቀብ እንዲጥሉ የሚፈቅድ እንደሆነም ይታወቃል።
በኬንያ፣ በሶማሊያ እና በአጎራባች ሀገራት አስካሁን ለደረሰው የሽብር ጥቃትና ለጠፋው የሰዎች ህይወት የቀጣናው ስጋት የሆነው አልሸባብ ተጠያቂ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ የነበረው ጉዳይ ነው፡፡
አሸባሪው ቡድን አሜሪካ እና አጋሮቿ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ለመፈጸም ማሴሩ አጠናክሮ እንደቀጠለበትም ይነገራል፡
በ1966 በሶማሊያ ሞቃዲሾ በሃውዋዳግ አውራጃ የተወለደው ራጊም ታዲያ በኬንያ እና ሶማሊያ የተፈጸሙትን ጥቃቶችን በማቀድና በማሴር ቁልፍ ሚና የነበረው ሰው መሆኑ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል አልሸባብን አሸባሪ ድርጅት ብላ በልዩ ሁኔታ የሰየመችው እንደፈረንጆቹ በመጋቢት 2008 እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሚያዝያ 2010ም አልሸባብ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የሶማሊያ ማዕቀብ ኮሚቴ በ1844ኛ የማዕቀብ መዝገብ ውስጥ የሰፈረበት ነበር፡፡