ትራምፕ ከካፒቶል አመጽ ጋር በተያያዘ ለታሰሩ 1500 አሜሪካውያን ፕሬዝደንታዊ ይቅርታ አደረጉ
የ2020ውን ምርጫ ውጤት ባለመቀበል ለአመጽ እንዲወጡ የጠሯቸው ደጋፊዎቻቸው በካፒቶል ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር መጋጨታቸው ይታወሳል
በዚህ ፖለቲካዊ ብጥብጥ 140 ፖሊሶች ሲጎዱ 4 ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ይታወሳል
ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ካገኙ ከጥቂት ሰአታት በኋላ ፍላጎቶቻቸውን ለማስፈጸም በፍጥነት ሲንቀሳቀሱ ከአራት አመት በፊት በካፒቶል ሂል ላይ ጥቃት ለፈጸሙት 1500 ደጋፊዎቻቸው ይቅርታ አድርገዋል።
ከበዓለ ሲመት ስነ ስርአቱ በኋላ ትራምፕ ስደትን ለመግታት ፣ የአካባቢ ጥበቃ ደንቦችን እና የዘር እና የሥርዓተ-ፆታ ብዝሃነት ለማሻሻል ተከታታይ የሥራ አስፈፃሚ እርምጃዎች በፊርማቸው ተግባራዊ እንዲሁን አዘዋል፡፡
የምርጫ ዘመቻው ቁልፍ ጉዳይ ሆነው ከዘለቁ አጀንዳዎች መካከል አንዱ የሆነውን የታሪፍ ጭማሪ ጉዳይ በትላንቱ የመጀመሪያ ቀን ቆይታቸው አልወሰኑም፤ ነገር ግን ከፌብሩዋሪ 1 ጀምሮ በካናዳ እና በሜክሲኮ ላይ 25 በመቶ ታሪፍ ጭማሪው ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የጥር 6 2021 በካፒቶል ላይ ጥቃት ያደረሱ ሁሉንም ተከሳሾች ይቅር ለማለት የወሰደቱ ውሳኔ ፖሊስን፣ ህግ አውጪዎችን እና ሌሎች በወቅቱ ህይወታቸው ለአደጋ ተጋልጦ የነበሩ ሰዎችን ማስቆጣቱ ተነግሯል፡፡
በጥቃቱ ወደ 140 የሚጠጉ ፖሊሶች ጥቃት ደርሶባቸዋል፣ አንዳንዶቹ ፊታቸው ላይ ኬሚካል ተረጭቶባቸዋል ብረት እና እንጨትን ጨምሮ በተለያዩ መሳሪዎች ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡
በወቅቱ በነበረው ግርግር በፖሊስ ጥይት የተገደለውን የትራምፕ ደጋፊን ጨምሮ የአራት ሰዎች ህይወት አልፏል።
ትራምፕ ከበአለ ሲመታቸው በፊት ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ በዚህ ፖለቲካዊ አመጽ ክስ የቀረበባቸውን ደጋፊዎቻቸው መካከል “የተወሰኑት ከመስመር አልፈዋል” በሚል ሁሉንም ይቅር እንደማይሉ ተናግረው ነበር፡፡
ትራምፕ ረጅም የእስር ቅጣት ያስተላለፈባቸው 14 የቀኝ አክራሪ “የመሃላ ጠባቂዎች እና ፕራውድ ቦይስ” ታጣቂ ቡድኖች መሪዎች ከእስር ቤት እንዲለቀቁ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ቃለ መሀላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት የመጀመሪያ ፕርዝዳንታዊ ንግግር "አሜሪካን እንደገና ታላቅ ለማድረግ በእግዚአብሔር ሁለተኛ እድል ተሰጥቶኛል" ያሉት ትራምፕ፤ ከ100 አመታት ወዲህ ከመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው በኋላ ተሸንፈው ወደ ነጩ ቤት የተመለሱ እንዲሁም በሁለቱም ምክር ቤቶች በሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው የመጀመሪያው መሪ ናቸው፡፡