የዶናልድ ትራምፕ የኋይት ሀውስ የመጀመሪያ ቀን ውሎ እና ተጠባቂ ውሳኔዎች
ፕሬዝዳንቱ በመጀመሪያ ቀን የስልጣን ጊዜያቸው ከ100 በላይ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዞችን ፈርመው ወደ ስራ እንደሚያስገቡ ይጠበቃል
ህገ ወጥ ስደት ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ንግድ እና ኢኮኖሚ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ትላልቅ ውሳኔዎች ከሚተላፍባቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ
አወዛጋቢው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ነጩ ቤተ መንግስት (ኋይት ሀውስ) ተመልሰዋል፡፡
ከሰአታት በኋላ በሚካሄደው በዓለ ሲመት ቃለ መሀላ ፈጽመው የሀያሏን ሀገር መሪነት የሚረከቡት ሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት በመጀመሪያ ቀን የስልጣን ቆይታቸው የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች እየተጠበቁ ነው፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ፖሊሲያቸውን ሲያስተዋወቁ በስፋት ቅስቀሳ ካደረጉባቸው ጉዳዩች መካከል፤ የስደተኞች እና ድንበር ጥበቃ ጉዳይ ፣ ንግድ ፣ ታሪፍ እና ኢኮኖሚ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ እና ሌሎች ወሳኝ እርምጃዎች በመጀመሪያ ቀን የስልጣን ቆይታቸው በስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ተፈርመው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡
-ህገወጥ ስደተኞችን ከሀገር ማስወጣት እና የድንበር ጥበቃ
ትራምፕ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በአሜሪካ ታሪክ ትልቅ የተባለውን ህገ ወጥ ስደተኞችን ከሀገር ማስወጣት ስራ ለማከናወን ቃል ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ብሔራዊ የድንበር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሀገሪቱ ጦር ደቡባዊ ድንበርን ለመጠበቅ እንዲሰማራ ትዕዛዝ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡
የኢሜግሬሽን ሃላፊዎች በቤተክርስቲያናት እና ትምህርት ቤቶች አሰሳ እና ፍተሸ እንዳያደርጉ የሚያግደውን ለረጅም ጊዜ የቆየውን ፖሊሲ እንደሚሰርዙም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም 70 ሺህ የሚጠጉ በሜክሲኮ የሚገኙ የጥገኝነት ጥያቄ አቅራቢዎች ባሉበት እንዲቆዩ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንቱ የአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪዎችን ከአልቃይዳ ፣ ከአይኤስ እና ከሀማስ ጎን “የውጭ አሸባሪዎች” በሚል እንደሚፈርጇቸውም ተነግሯል፡፡
የሜክሲኮ አሜሪካ ድንበር አጥርን መገንባት ፣ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ማስቆም እና ደቡባዊ አሜሪካን ከሜክሲኮ ጋር የሚያገኛኝውን ድንበር መዝጋት በስደተኞች እና ድንበር ፖሊሲ ስር በመጀመሪያ ቀን ከሚያስፈጽሟቸው ውሳኔዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
-ንግድ እና ኢኮኖሚ
ትራምፕ ለአሜሪካ አምራቾች ቅድሚያ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ከተለያዩ ሀገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
በአዲሱ መንግስታቸው ከሁሉም ሀገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ቃል የገቡት ፕሬዝዳንቱ ከካናዳ እና ሜክሲኮ በሚገቡት ላይ ደግሞ ታሪፉ 25 በመቶ እንዲሆን ወስነዋል፡፡
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከቻይና ጋር የተካረረ የንግድ ጦርነት ውዝግብ ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ 60 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ እና ይህንንም ለማስፈጸም በመጀመሪያ ቀን የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ እንደሚፈርሙ ተናግረዋል፡፡
የታሪፍ ጭማሪው የሸቀጦችን ዋጋ ሊያንረው እንደሚችል እና የዋጋ ንረቱንም እንደሚያባብሰው ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ትራምፕ በዚህኛው የስልጣን ዘመናቸው ትኩረት ይሰጡታል ተብሎ የሚጠበቀው ክሪፕቶ ወይም ዲጂታል ገንዘብ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ የወርቅ እና የነዳጅ ክምችት እኩል የፌደራል የቢትኮይን ክምችትን ዕውን ለማድረግ ሊሰሩ ይችላ ተብሏል፡፡
-የአየር ንብረት ለውጥ እና ኢነርጂ
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደስኬት ከሚነገሩላቸው ተግባራት መካከል የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ተግባራዊ ያደረጓቸው ህጎች ፣ የገንዘብ ድጋፎች እና መመሪያዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
አዲሱ ፕሬዝዳንት እነኚህን ህጎች በመጀመሪያ ቀን ቆይታቸው ለመሻር እንዲሁም በባህር ዳርቻ እና በፌደራል መሬቶች ላይ የሚደረጉ የነዳጅ ቁፋሮዎችን የሚገድበውን ህግ ለመሰረዝ ቃል ገብተዋል፡፡
በተጨማሪም በ2017 ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ለመውጣት ያሳለፉትን ውሳኔ ለማጽናት እና ባይደን ከ2021 ጀምሮ ወደ ስምምነቱ ለመመለስ ሲያደርጉ የነበሩትን ጥረት እንደሚያስቆሙ ይጠበቃል፡፡
-የካፒቶል ሂል አመጽ
ከ2021 የአሜሪካ ካፒቶል ሂል ግርግር ጋር በተያያዘ ተከሰው የተፈረደባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ብጥብጥ ጋር በተገናኘ ከ1500 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 600 ያህሉ የፌደራል ሰራተኞች ላይ ጥቃት በማድረስ ተከስዋል፤ ከነዚህ ተከሳሾች መካከል ለተወሰኑት ፕሬዝዳንታዊ ይቅርታ እንደሚደረግላቸው ይጠበቃል፡፡
-የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ
የዩክሬን ሩስያ ጦርነትን በ24 ሰአታት ውስጥ አስቆማለሁ በሚል በተደጋጋሚ ሲናገሩ የተደመጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሁን ላይ ጦርነቱን ለማስቆም 6 ወራት ሊፈጅ እንደሚችል አምነዋል፡፡
ነገር ግን በመጀመሪያ ቀን የስልጣን ጊዜያቸው ከጦርነቱ ጋር አንዳች ውሳኔን ሊያሳልፉ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ትራምፕ ባይደን በቅርቡ ኩባን ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ድጋፍ ሰጪዎች ዝርዝር ውስጥ ለማስወገድ ያሳለፉትን ውሳኔ እንደሚቀለብሱ እንዲሁም በቬንዙዌላ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ወደነበረበት ሊመልሱ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ጽንስ መቋረጥ ፣ በመንግስት እጅ ብቻ የነበሩ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ይፋ ማድረግ ፣ ጾታ የቀየሩ ዜጎች ጉዳይ እና ሌሎችም በትራምፕ የመጀመሪያ ቀን የነጩ ቤት ቆይታ ውሳኔ ከሚተላለፍባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀሱ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡