"ሁሉም ሀብታም ሰዎች በቲክቶክ ጉዳይ ደውለውልኛል" - ትራምፕ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በቲክቶክ ላይ የተጣለው እገዳ ተፈጻሚነት በ75 ቀናት እንዲራዘም ወስነዋል
በቲክቶክ ከ15 ሚሊየን በላይ ተከታይ ያላቸው ትራምፕ በ2020 የቻይናውን መተግበሪያ ለማገድ መሞከራቸው የሚታወስ ነው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በባይደን አስተዳደር ታግዶ አገልግሎት አቁሞ የነበረውን ቲክቶክ እንዲከፈት የሚያስችል የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈረሙ።
ፕሬዝዳንቱ ትናንት ምሽት ባሳለፉት ውሳኔ ቲክቶክ ላይ የተጣለው እገዳ ተፈጻሚነት በ75 ቀናት እንዲራዘም አድርገዋል።
በእነዚህ ቀናት ባለፈው አመት በኮንግረንሱ የጸደቀው ህግ እና በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ እንደማይሆንም ነው የተገለጸው።
የፕሬዝዳንታዊ ውሳኔው ቲክቶክ በ75 ቀናት ውስጥ ለአሜሪካ ባለሀብቶች ካልተሸጠ ሊዘጋ እንደሚችል የሚያመላክት ቢሆንም ለ170 ሚሊየን አሜሪካውያን የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች እና ለቻይናው ኩባንያ እፎይታ የሰጠ ነው ተብሏል።
በነጩ ቤተመንግስት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት ትራምፕ "ሁሉም ሀብታም ሰው በቲክቶክ ጉዳይ እንደደወለልኝ ልነግራችሁ እወዳለሁ" ብለዋል።
በ2020 የባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነውን ቲክቶክ ለመዝጋት ጥረት ያደረጉት የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት "አቋምዎን ምን አስቀየረዎ?" ተብለው ሲጠየቁ "ምክንያቱም ተጠቅሜበታለኋ!" የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
ትራምፕ የ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲቃረብ የከፈቱት የቲክቶክ አካውንት ከ15 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን አግኝቷል፤ የለቀቋቸው ቪዲዮዎችም ከ60 ቢሊየን በላይ ተመልካች እንዳገኙ የቲክቶክ ስራ አስፈጻሚ ሱዚ ቼው መናገራቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ እና የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ እኩል 50 በመቶ ድርሻ ይዘው ሊያስተዳድሩት እንደሚችሉ ቢገልጹም ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር ተቆጥበዋል።
የባይደን አስተዳደር ቻይና ቲክቶክን ለስለላ ልትጠቀምበት ትችላለች በሚል ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት መተግበሪያው በአሜሪካ መስራት ማቆሙ ይታወሳል።
ትራምፕ ዋይትሃውስ እንደገቡ እገዳውን እንደሚያነሱ መናገራቸውን ተከትሎም ቲክቶክ ዳግም መስራት ጀምሯል።
ፕሬዝዳንቱ ያሳለፉት ውሳኔ በርካታ የኮንግረንሱ አባላትም ሆነ በፓርቲያቸው ተቃውሞ እየገጠመው ነው።
ሪፐብሊካኑ ሴናተር ቶም ኮተን "(በቻይና) ኮሚዩኒስት ፓርቲ ቁጥጥር ስር ያለውን ቲክቶክ የሚያስተናግድ፣ አገልግሎቱን የሚያግዝና የሚያሰራጭ የትኛውም ኩባንያ በመቶዎች ቢሊየን ዶላር ቅጣት ይጠብቀዋል" ብለዋል።
በትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙት የቲክቶክ ስራ አስፈጻሚ ሹ ዚ ቸው በበኩላቸው የሚቀርቡ ወቀሳዎችን በማጣጣል ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።
የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤለን መስክ እና ታዋቂውን ዩቲዩበር "ሚስተር ቢስት" ጨምሮ በርካታ ኩባንያዎች እና ቢሊየነሮች ቲክቶክን ለመግዛት ጥያቄ ማቅረባቸው ተዘግቧል።