በፈረንሳይ መነጋገሪያ የሆነው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ "ሿሿ"
የ53 አመቷ ፈረንሳዊት "ብራድ ፒት" ነኝ ብሎ በቀረባት ግለሰብ 850 ሺህ ዶላር ተጭበርብራለች
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በኦንላይን ላገኘችው ሰው በህይወት ዘመኗ ያጠራቀመችውን ገንዘብ በላከችው እንስት ላይ እየተሳለቁባት ነው
የ53 አመቷ ፈረንሳዊት "ብራድ ፒት" ነኝ ብሎ በቀረባት ግለሰብ 850 ሺህ ዶላር መጭበርበሯ መነጋገሪያ ሆኗል።
አን የተሰኘችው ዲዛይነር ከታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ ጋር ለአንድ አመት ተኩል ያህል የፍቅር ግንኙነት ውስጥ እንዳለች ብታምንም ግንኙነቷ ከትክክለኛው ብራድፒት ጋር ሳይሆን "ኤአይ ብራድ ፒት" ጋር መሆኑን አረጋግጣለች።
ግለሰቧ ሶስት ጊዜ ራሷን ለማጥፋት ሞክራ በእኔ የሆነው በሌሎች እንዳይደገም በሚል ወደ ሚዲያ ቀርባለች።
በአንድ ታዋቅ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ቀርባም "እብድ አይደለሁም፤ እንደተጨበረበርኩ አምናለሁ፤ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ ስለማውቅ ግን ወጥቼ አውርቻለሁ" ብላለች።
ቲኤፍ1 የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያን ጨምሮ የተለያዩ የፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን በአን መጭበርበር ዙሪያ ዘገባዎችን መስራታቸውን ተከትሎም ትችቱ በዝቶባታል።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም እንዴት በኦንላይን ላገኘችው ሰው በህይወት ዘመኗ ያጠራቀመችውን ገንዘብ ትልካለች? በሚል የተለያዩ የፌዝ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
ኔትፍሊክስ ፍራንስ በኤክስ ገጹ "አራት ፊልሞች ከብራድ ፒት ጋር (በእርግጥም)" የሚል ጽሁፍ አውጥቶ በአን ላይ ተሳልቋል።
ቱሉዝ እግርኳስ ክለብም "ሰላም አን ብራድ ፒት ረቡዕ ወደ ስታዲየማችን ይመጣል፤ አንቺስ?" የሚል የፌዝ ጽሁፍ አውጥቶ የነበረ ሲሆን፥ ይቅርታ ጠይቆ መልዕክቱን አንስቶታል።
የብራድ ፒት ተወካይ ለኢንተርቴይንመንት ዊክሊ በሰጡት አስተያየት "አጭበርባሪዎች አድናቂዎች ከታዋቂ ሰዎች ጋር ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት እንደ እድል በመጠቀም መበዝበዛቸው አሳዛኝ ነው" ብለዋል።
ሰዎች በተለይ ምንም አይነት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የሌላቸው ታዋቂ ግለሰቦች መስለው የሚቀርቡ አጭበርባሪዎችን እንዲጠነቀቁም አሳስበዋል።
"የኤአይ ብራድ ፒት" ሿሿ መቼና እንዴት ተካሄደ?
አን በየካቲት ወር 2023 ኢንስታግራም ስታወርድ ነው የዚሁ ሁሉ ነገር መነሻ። በወቅቱ ከሃብታም ባሏ ጋር በትዳር ውስጥ የነበረችው ፈረንሳዊት ኢንስታግራም እንደከፈተች የብራድ ፒት እናት ነኝ ከሚሉ (ጃን ኢታ) መልዕክት ይደርሳታል። "ልጄ እንዳንቺ አይነት ሴት ያስፈልገዋል የሚል።
በቀጣዩ ቀንም ብራድ ፒትን የመሰለ ሰው ቀርቦ ያናግራታል። "ማህበራዊ ሚዲያ ብዙም የምጠቀም ሰው ስላልሆንኩ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አላውቅም ነበር" ስትልም ታወሳለች።
"ብራድ ፒት" ነኝ ያለው ግለሰብ በሌላ ጊዜም ለአን ውድ ስጦታዎችን ሊልክላት ማሰቡን ነገር ግን ከአንጀሊና ጆሊ ጋር ባለበት የፍቺ ሂደት የባንክ ሂሳቡ መታገዱን ጠቅሶ 9000 ዩሮ ያስልካታል።
የ53 አመቷ ጎልማሳ "ሁሌም እጠራጠረዋለሁ፤ ግን እንደ ጅል ዝም ብዬ እልክለታለሁ፤ ጥርጣሬየን በፍጥነት ማጥፋቱን ተክኖበታል" ብላለች።
የገንዘብ ጥያቄው እየጨመረ የሄደው ሀሰተኛው ብራድ ፒት የኩላሊት ካንሰር ታማሚ ነኝ ማለት ሲጀምር ነው።
ግለሰቡ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተሰሩና ብራድ ፒት ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ ሲታከም የሚያሳዩ ምስሎችንም ይልክላታል።
በዚህ ጊዜ አን ከባለቤቷ ጋር ፍቺ ፈጽማ 775 ሺህ ዩሮ ደርሷት ነበርና "የአንድ ሰውን ህይወት ልታደግ" በሚል ምንም ሳታስቀር ለአጭበርባሪው ልካለታለች። ፍቺውን እንድትፈጽም የማግባባቱን ስራውም በሚገባ ተወጥቷል።
አን ለአንድ አመት ተኩል የፍቅር አጋሯ አድርጋ የምትመለከተው ትክክለኛው ብራድ ፒት አለመሆኑ የገባት ተዋናዩ ከኢነስ ደ ራሞን ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዳለው መነገር ከጀመረ በኋላ ነው።
ለአጭበርባሪው ይህን ስትነግረውም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቴክኖሎጂ የተቀነባበረ ዜና ልኮላታል፤ የኤአይ ዜና አንባቢው ብራድ ፒት "ከአንዲት የተለየች ሴት ጋር የፍቅር ግንኙነት አለው፤ እርሷም አን ትባላለች" ሲል ይደመጣል።
ቪዲዮው ለአጭር ጊዜም ቢሆን እፎይታ ቢሰጣትም ብራድ ፒት እና ኢነስ ደ ራሞን በሰኔ ወር 2024 ግንኙነታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ወሽመጧን ቆርጦታል።
850 ሺህ ዶላር የተጭበረበረችው ፈረንሳዊት አሁን ከጓደኛዋ ተጠግታ አሳዛኝ ህይወት ለመኖር መገደዷን ተናግራለች።