አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለኢትዮጵያ ቅንጦት ወይስ አስፈላጊ ነው?
ትኩረቱን በአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ያደረገ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረተ ልማቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ቅንጦት ነው ሲባል በሌላ በኩል ደግሞ ዓለም ላትመለስ ፊቷን ወደ ኤአይ አዙራለች የሚሉ አሉ
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለኢትዮጵያ ቅንጦት ወይስ አስፈላጊ ነው?
ሶተኛው የፓን አፍሪኮም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጉባኤ በአዲ አበባ ተካሂዷል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ላይ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የተቋማት አመራሮች፣ ተመራማሪዎች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው እየተሳተፉ ካሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት እና የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ባለሙያው ዳግማዊ ቴድሮስ ከአል-ዐይን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ቅንጦት ነው ብለዋል፡፡
በአሜሪካ የኤአይ መሰረተ ልማት ሙያ መስክ መሰማራታቸውን የሚናገሩት ዳግማዊ “ትላልቆቹ የኤአይ ኩባንያዎች በማንኛውም የአፍሪካ ሀገር የሉም፡፡ አሁን አሁን ኤአይ የሚለውን ቃል ማንኛውም ሰው ሲጠራው እሰማለሁ፡፡ ይህ ችግር ላይሆን ይችላል፣ ነገር ግን መጀመሪያ ቴክኖሎጂውን መረዳት፣ ምን ይፈልጋል፣ እንዴት እንጠቀምበት በሚለው ላይ በሚገባ መሰራት አለበት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኢንተርኔት፣ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች አልተሟሉም ኤአይ ደግሞ ቢያንስ ከነዚህ ባለፈ እንደ ግዙፍ የዳታ ማዕከላት፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን እንደሚፈልግም ዳግማዊ አክለዋል፡፡
ኤአይ የተቋማትን ውጤታማነት በማሳደግ አገልግሎቶችን ያለ ማቋረጥ በጥንቃቄ መስራት ያስችላል ጠየሚሉት ዳግማዊ ይህ የሚሆነው ግን መሰረተ ልማቶች ሲሟሉ ብቻ ነውም ብለዋል፡፡
ይሁንና ኤአይ አይጠቅምም ተብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይገባም የሚሉት ዳግማዊ ሁሉም ሰው ስለ ኤአይ ከማውራት ይልቅ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ ግፊት ማድረግ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ሁሉም ሀገር የራሱን ኤአይ ቴክኖሎጂ እያበለጸገ ነው፣ አሁን አያስፈልገንም ብለን ቁጭ ካልን የሀገራት ተከታይ ሆነን እንቀራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር ኢትዮጵያ የራሷን ቋንቋዎች የማሽን ቋንቋዎች እንዲሆኑ ካላደረገች ሌሎች ሀገራት ጥለውን ይሄዳሉ ተቋሞቻችንም ቀስ በቀስ ውጤታማ እንዲሆኑ ካላደረግን ሁሌም የሀገራት ተከታይ ሆነን እንቀራለን ሲሉም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሶማሊ እና ትግሪኛ ቋንቋዎች የማሽን ቋንቋዎች እንዲሆኑ እያደረግን ነው፣ ቴክኖሎጂውን ከኢትዮጵያ ሁኔታ አንጻር ለመጠቀም እየሞከርን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተቋማት ኤአይን ተጠቅመው አገልግሎት የመስጠት ጥራታቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ መሆኑን ወርቁ ጋቸና ገልጸዋል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፣ፌደራል ፖሊስ፣ ጸረ ሙስና ኮሚሽን እና ሌሎችም ተቋማት ኤአይን ተጠቅመው አገልግሎታቸውን እያቀላጠፉ እና እያዘመኑ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ለአብነት አንስተዋል፡፡
መረጃዎችን ቀድሞ ያደራጀ እና የመዘገበ ሀገር ሁሌም አሸናፊ ሆናል የሚሉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ኢትዮጵያ እስካሁን ኤአይ ከሚፈልጋቸው መሰረተ ልማቶች መካከል ዋነኛ የሆኑት የዳታ ማዕከላት እና የሰለጠነ የሰው ሀይል ላይ በስፋት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም 15 ፔታ ባይት ክላውድ መረጃ መያዝ የሚችል የመረጃ ማዕከል ከመገንባቱ ባለፈ የኢትዮጵያ ትምህርት ተቋማት ከአጫጭር ስልጠናዎች እስከ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ድግሪ ድረስ የኤአይ ስልጠናዎችን እና ምርምሮችን እያደረጉ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለፈ የፋይናንስ ተቋማትም ኤአይ እንዲጠቀሙ እና አገልግሎቶቻቸውን እንዲያዘምኑ እያደረግን ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኤአይን እንደ ቅንጦት ሳይሆን እንደ አንድ የእድገት ካታሊስት አድርጋ እንደምትወስደውም ተገልጿል፡፡
በርካታ የዓለማችን ሀገራት የየራሳቸውን ኤአይ እየተሽቀዳደሙ እያስተዋወቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የየትኛውን ሀገር ኤአይ ቴክኖሎጂን እንደ መነሻ ትወስዳለች? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “አሜሪካም ሆነ አውሮፓ እንዲሁም ቻይና ሩሲያ እና ሌሎችም ሀገራት የየራሳቸውን እያበለጸጉ ነው፡፡ እኛ እንደ ሀገር ከዚህኛው ሀገር ነው የምንወስደው አንልም፡፡ የሚጠቅመንን ልምድ ከሁሉም ሀገር እየወሰድን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በርካታ ሀገራት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ለማስፋት በሚኒስቴር እና ኢንስቲትዩት ደረጃ እያደራጁ ሲሆን ኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በፈረንጆቹ 2020 ላይ ማቋቋሟ ይታወሳል፡፡
ፈረንሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤአይ ሚኒስትር ከአንድ ወር በፊት መሾሟ አይዘነጋም፡፡