አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የ300 ሚሊየን ሰዎችን የሙሉ ጊዜ ስራ ሊተካ እንደሚችል ተነገረ
ቴክኖሎጂው በአሜሪካ እና አውሮፓ ስራ ላይ ካሉ ሰዎች የሩቡን በመተካት ሚሊየኖችን ከስራ ውጭ ሊያደርግ ይችላልም ተብሏል
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሊቆጣጠራቸው የሚችሉ የስራ ዘርፎች እየጨመሩ መሄዳቸው እየተነገረ ነው
የሰው ሰራሽ ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ 300 ሚሊየን የሚደርስ የሰው ልጆችን የሙሉ ጊዜ ስራ ተክቶ መስራት ይችላል ተባለ።
አለምአቀፉ የኢንቨስትመንት ባንክ ጎልድማን ሳችስ ያወጣው ሪፖርት ፥ በአሜሪካ እና አውሮፓ በሰው ልጆች እየተከወኑ ከሚገኙ ስራዎች ውስጥ ሁለት ሶስተኛው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሊተካ እንደሚችል ያሳያል።
ቴክኖሎጂው በቅርብ አመታት ውስጥ በአሜሪካ እና አውሮፓ አሁን ላይ ስራ ላይ ካሉ ሰዎች የሩቡን ተክቶ ሚሊየኖችን ስራ ሊያሳጣ እንደሚችልም ነው የባንኩ ጥናት ያመላከተው።
ጥናቱ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጆችን ስራ ከመንጠቅ ይልቅ በአዳዲስ የስራ ዘርፎች ተሰማርቶ ምርታማነትን ለማሳደግ ያለውን ትልቅ ድርሻም ያሳየ ነው።
የባንኩ ጥናት የሰው ሰራሽ አስተውሎት መስፋፋት በአለምአቀፍ ደረጃ አመታዊ የሸቀጦች ምርት እና አገልግሎትን በ7 በመቶ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል ይላል።
እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች የሰው ልጆች ሊሰጡት የሚችሉት አይነት ፈጣን መልስ እየሰጡ ነው።
የተወሰነ መረጃን በመስጠት ብቻ ረጃጅም ጽሁፎችን እና መጣጥፎችን ማዘጋጀት መቻሉም በአርት ዘርፍ የተሰማሩ እንደ ጋዜጠኝነት ያሉ ሙያተኞችን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ መክተት ጀምሯል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚሰሩ የአርቲስቶች ምስሎችም ከትክክለኛው መለየት እስኪከብድ ድረስ ተመሳሳይ እየሆነ መሄድ የትወና ባለሙያዎችን በማሳሰብ ላይ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቧል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መበራከትም የሾፌሮች አስፈላጊነትን እየቀነሰው መሄዱ ተነግሯል።
ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት ቢሊየን ዶላሮችን የምትመድበው ብሪታንያ፥ ቴክኖሎጂው ምርታማነትን እንዲያሳድግ እንጂ ሰዎችን ስራ እንዲያሳጣ አንፈልግም ብላለች።
የሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሚሸል ዶኔላን ፥ ሰዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት መስፋፋት ስጋት ሊሆንባቸው አይገባም ሲሉ ለዘ ሰን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ይህን ይበሉ እንጂ ከ1980ዎቹ ጀምሮ የተቀጣጠለው የቴክኖሎጂ አብዮት ከሚፈጥረው የስራ እድል ይልቅ ስራ አጥ የሚያደርገው እየበለጠ መሄዱን ነው ጥናቶች የሚያሳዩት።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከሚቆጣጠራቸው የስራ ዘርፎች መካከል 46 ከመቶው አስተዳደራዊ 44 ከመቶው ደግሞ የህግ ዘርፍ ይሆናል ነው የተባለው።
የግንባታ እና የጥገና ዘርፎች ግን በሰው ሰራሽ አስተውሎት የመተካት እድላቸው አነስተኛ እንደሚሆን ጎልድማን ሳችስ ባንክ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።