የረሃብ አደጋን የሚተነብየው የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ሲስተም
የአሜሪካው ኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በአለም ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ የምግብ ቀውሶችን ከ12 ወራት በፊት የሚጠቁም የኮምፒውተር ስርአት አስተዋውቋል
በ40 ሀገራት የተከሰቱ አደጋዎችን የተመለከቱ ከ11 ሚሊየን በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች እና ዜናዎች ለትንበያው ግብአት ናቸው ተብሏል
ተመራማዎች በአለማችን የሚከሰቱ የምግብ ቀውሶችን አስቀድሞ የሚጠቁም አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ወይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርአት ፈጠሩ።
ስርአቱ በተለያየ ጊዜ የወጡ መግለጫዎች እና የዜና ጥንቅሮችን መሰረት አድርጎ ትንበያውን ያስቀምጣል ተብሏል።
- ኢትዮጵያ እና ዩኤኢ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ተወያዩ
- የአውሮፓ ሕብረት፤ በአውሮፓ በ 500 ዓመት ውስጥ “አስከፊ” የተባለ ድርቅ መከሰቱን ገለጸ
በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የኮራንት የሂሳብ ትምህርት ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች የበለጸገውና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅሞ ትንበያውን ያስቀምጣል የተባለው የመረጃ ስርአት፥ ድርቅን ጨምሮ የምግብ ቀውስ የሚያስከትሉ አደጋዎችን ይጠቁማል።
ይህም አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ፈጣኖ ለመድረስ እንደሚያስችል ነው ተመራማሪዎቹ ያነሱት።
አዲሱ ሳይንሳዊ ስርአት በአለም ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ የረሃብ አደጋዎችን ከ12 ወራት በፊት እንደሚያመላክት ሳሙኤል ፍሬበርግ የተባለ የጥናቱ ተሳታፊ ተናግረዋል።
የጥናት ቡድኑ ለዚህ የመረጃ ጠቋሚ ስርአት ግብአት የሚሆኑ የምግብ ቀውስ ላይ ያተኮሩ ከ11 ሚሊየን በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች እና ዜናዎችን ሰብሰብዋል።
ከፈረንጆቹ 1980 እስከ 2020 በ40 ሀገራት የተከሰቱ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ያስከተሏቸውን የረሃብና የምግብ ቀውስ ችግሮች የተመለከቱት መረጃዎች እንዲገቡ ተደርገዋል።
በነዚህ ዘገባዎች እና ጥናታዊ ጽሁፎች ውስጥ የምግብ ቀውስን ያመላክታሉ የተባሉ ቃላትና ሀረጋትም በኮምፒውተር ስርአቱ ውስጥ መግባታቸውን ነው ተመራማሪዎቹ ያነሱት።
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሚጠቀመው ስርአትም እነዚህን መረጃዎች እየተነተነ በመላው አለም ሊከሰቱ ስለሚችሉ የድርቅ እና የረሃብ አደጋዎች ይተነብያል ተብሏል።
የኮምፒውተር ስርአቱ ከዚህ ቀደም በባህላዊ መንገድ የሚደረገውን የምግብ ቀውስ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን የመለየትና የዘገየ ምላሽ የመስጠት ችግር እንደሚያስቀር ታምኖበታል።
በአሁኑ ወቅት ሀገራት ለሚገጥማቸው የምግብ ቀውስ ምላሽ የሚሰጡት የበርካቶች ህይወት አልፎ እጅግ ዘግይተው ነው።
አዲሱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ግን ከአንድ አመት በፊት ትንበያውን የሚያመላክት በመሆኑ ሀገራት ቀድመው እንዲዘጋጁ በማድረግ ሰብአዊ ቀውሱን እንዲቀንሱ ያስችላቸዋል ነው ያሉት ላክሽሚን አራያና የተሰኙት ሌላኛው የጥናቱ ተሳታፊ።
የጥናት ቡድኑ በቀጣይም መሰል ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቅም አዳዲስ ወረርሽኞችን እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን መተንበይ እንደሚቻል መግለጹንም ነው ሜዲካል ኤክስፕረስ ድረገጽ ያስነበበው።