በ2022 ኢንተርኔትን የዘጉ ሀገራት ቁጥር በክብረወሰንነት ተመዘገበ
የኢንተርኔት መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያወጡት መረጃ እንደሚያሳየው፥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 35 ሀገራት ኢንተርኔትን ለረጅም ጊዜ ዘግተዋል
ተቃውሞዎች፣ ምርጫ እና ብሄራዊ ፈተናዎች ኢንተርኔት እንዲዘጋ ምክንያት ሆነዋል ተብሏል
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ኢንተርኔት የዘጉ ሀገራት ቁጥር በክብረወሰንነት መመዝገቡን የኢንተርኔት መዘጋትን እየተከታተሉ የሚመዘግቡ ተቋማት አስታውቀዋል።
“አክሰስ ናው” እና “ኪፕ ኢት ኦን” የተሰኙት ተቋማት በጋራ ባወጡት ሪፖርት፥ በ2022 35 ሀገራት ኢንተርኔትን መዝጋታቸውን አመላክተዋል። በነዚህ ሀገራት 187 ጊዜ ኢንተርኔት መዘጋቱንም በመጠቆም።
ህንድ በ2022 84 ጊዜ ኢንተርኔትን በማቋረጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።
በተደጋጋሚ ኢንተርኔት የተዘጋባቸው አካባቢዎችም አወዛጋቢዎቹ የጃሙ እና ካሽሚር ክልሎች መሆናቸውን ያነሳው ሪፖርቱ፥ ኢንተርኔትን የመዝጋት ልማዱ ወደሌሎች አካባቢዎችም እየተዳረሰ ነው ብሏል።
22 ጊዜ ኢንተርኔት የተቋረጠባት ዩክሬን ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። በሩሲያ የሚፈጸሙ የሚሳኤል እና የሳይበር ጥቃቶችም በዩክሬን ተደጋግሞ ለተከሰተው የኢንተርኔት መቋረጥ በምክንያትነት ተነስቷል።
ህዝባዊ ተቃውሞዎች የተበራከተባት ኢራንም በ2022 18 ጊዜ ኢንተርኔት ማቋረጧ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በማይናማር ሰባት ጊዜ፤ በባንግላዲሽ ደግሞ ስድስት ጊዜ ኢንተርኔት የተቋረጠ ሲሆን፥ በዮርዳኖስ፣ ሊቢያ፣ ሱዳን እና ተርከሚኒስታን አራት አራት ጊዜ ኢንተርኔት መቋረጡ በጥናቱ ተጠቅሷል።
በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል ለሁለት አመት ኢንተርኔት ተቋርጦባት በነበረችው ኢትዮጵያ በ2022 ከብሄራዊ ፈተና ጋር በተያያዘ ኢንተርኔት መዘጋቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ 18 ሀገራት ቢያንስ አንድ ጊዜ ኢንተርኔት የተቋረጠባቸው ሲሆን፥ አፍጋኒስታንን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ደግሞ ሁለት ሁለት ጊዜ ኢንተርኔት ዘግተዋል ይላል ሪፖርቱ።
መንግስታት ኢንተርኔትን ለመዝጋት ተቃውሞዎችን፣ ምርጫ እና ብሄራዊ ፈተናዎችን እንደምክንያት ያስቀምጣሉ ያለው አክሰስ ናው፥ “አምባገነኖቹም ሆኑ ዴሞክራሲን እየተለማመዱ ያሉት መንግስታት ኢንተርኔትን በመዝጋት ድምጽን የማፈን አባዜ ተጸናውቷቸዋል” ብሏል።
ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው በ16 ሀገራት በተነሱ ተቃውሞዎች ምክንያት 62 ጊዜ ኢንተርኔት ተዘግቷል።
በስድስት ሀገራት ብሄራዊ ፈተናዎችን ከስርቆት ለመከላከል በሚልም ስምንት ጊዜ ኢንተርኔት መዝጋት ብቻኛው አማራጭ ሆኗል ነው የሚለው የአክሰስ ናው እና ኪፕኢትኦን የጋራ ሪፖርት።
በ14 ሀገራት 48 ጊዜ ኢንተርኔት ሲዘጋም ግልጽ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የመብት ጥያቄዎች እንዲታፈኑ ተደርጓል ሲልም ያክላል።
አምስት ሀገራትም ከምርጫ ጋር በተያያዘ አምስት ጊዜ ኢንተርኔት ዘግተዋል ተብሏል።
በ2022 ከተመዘገቡት ውስጥ 16ቱ ከ2021 የቀጠሉ መሆናቸውም ኢንተኔት ተዘግቶ የሚቆይበት ጊዜ ረጅም እየሆነ መምጣቱን እንደሚያሳይ ተብራርቷል።
በ2023ትም ይሄው የመንግስታት ተቃውሞዎችን ኢንተርኔትን በመዝጋት የማዳፈን ጥረት መቀጠሉ ነው የተነገረው።