በ2030 በአለም አቀፍ ደረጃ ከ93 ሚሊየን በላይ ሰራተኞች በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደሚተኩ ሪፖርት አመላከተ
የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም ባወጣው ሪፖርት በአስርት አመታቱ መጠናቀቂያ 41 በመቶ ቀጣሪዎች የሰራተኛ ቁጥራቸውን ለመቀነስ አቅድዋል ብሏል
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የሰው ልጅ በስራ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን ክህሎት ሊያዳብር እንደሚገባ መክረዋል
የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በሰፊው መሰማራት በአለም አቀፍ የስራ ገበያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እና በአለም አቀፍ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ የስራ ቅነሳን ሊያስከትል እንደሚችል ጥናት አመላክቷል፡፡
ከሰሞኑ ይፋ የሆነው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም “የመጪው ጊዜ የስራዎች ጥናት” በዓለም ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትላልቅ ቢዝነሶችን እና ኩባንያዎችን ዳሷል፡፡
ከዚህ ውስጥ 41 በመቶ የሚሆኑ ኩባንያዎች እያደገ የመጣውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት የስራ ተሳትፎ እና አቅም መዳበር መነሻ በማድረግ በ2030 በርካታ ሰራተኞቻቸውን ሊቀንሱ እንደሚችሉ የጥናቱ ውጤት ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም 77 በመቶ የሚሆኑ ኩባንያዎች ከ 2025 እስከ 2030 ድረስ ባሉት አመታት ሰራተኞቻቸው ከማሽኖች ፣ ሮቦቶች እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር እንዴት ተቀናጅተው መስራት እንደሚችሉ የተለያዩ የአቅም ማሳደጊያ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እያደረጉ ነው፡፡
በአስር ዓመቱ መጨረሻ (2030) 170 ሚሊየን አዳዲስ የስራ እድል እንደሚፈጠሩ የተነበየው ሪፖርቱ፤ 92 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ከስራ ገበታቸው እንደሚፈናቀሉ አሳስቧል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በመረጃ እና በሳይበር ደህንነት ስራዎች ላይ የሚኖረው ተፈላጊነት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻቅብ ነው የገለጸው፡፡
በአለም ኢኮኒሚክ ፎረም የስራ ፣ ደሞዝ እና የስራ ፈጠራ ኃላፊ የሆኑት ቲል ሊዮፖልድ በኢንዱስትሪ እና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ኤአይ የሚኖረው ተፈላጊነት ታይተው የማይታወቁ እድሎችን እና አደጋዎችን የሚያስከትል ነው ብለዋል፡፡
በ ኤአይ ፣ ሮቦቲክስ እና ኢነርጂ ስርአቶች በተለይም በታዳሽ ሃይል እና የአካባቢ ምህንድስና ውስጥ ያሉ እድገቶች በእነዚህ መስኮች የልዩ ባለሙያ ሚናዎችን እንደሚጠይቁ ሀላፊው አክለዋል፡፡
ሪፖርቱ በተጨማሪም በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች እድገት ምክንያት ከፍተኛ የስራ እድል እጥረት የሚያጋጥማቸው የስራ ምድቦች ለይቷል፡፡
ከነዚህ ውስጥ የአገልግሎት ዘርፍ ሰራተኞች፣ ዋና ፀሃፊዎች፣ የሂሳብ አዋቂዎች እና ግራፊክ ዲዛይነሮች ይገኛሉ፡፡
የ ኤአይ ተፅእኖ ከስራ መፈናቀል ባለፈ የሚዘልቅ መሆኑን ሪፖርቱ አፅንዖት ሰጥቶ፤ ቴክኖሎጂው የሰውን ልጅ በቀጥታ ከመተካት ባለፈ የፈጠራ አስተሳሰብ፣ ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ፣ ተለዋዋጭነት እና ቅልጥፍና ወሳኝ ሆነው እንደሚቀጥሉ ደምድሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቴክኖሎጂ ሰዎች እና ተመራማሪዎች የሰው ልጅ በስራ ገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን ክህሎት ሊያዳብር እንደሚገባ መክረዋል፡፡