የአሜሪካ ኮንግረስ በአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ድምጽ ሰጠ
ኮንግረሱ በፍርድ ቤቱ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የወሰነው በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ባወጣው የእስር ማዘዣ ነው
ማዕቀቡ በፍርድቤቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ተቋማት ላይ እንደሚያነጣጥር ተነግሯል
አሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት(አይሲሲ) ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚጠይቀውን የውሳኔ ሀሳብ አጸደቀ፡፡
የውሳኔ ሀሳቡ በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባላስልጣናት እና ተቋማዊ ንብረቶች ላይ ማዕቀብ የሚያሳልፍ ሲሆን በአሜሪካውያን እና በአጋሮቿ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ የሚሰሩ አካላትን በቀጥታ ይመለከታል ተብሏል፡፡
መቀመጫውን በኔዘርላንድ ሄግ ያደረገው አለምአቀፋዊው ተቋም በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮአቭ ጋላንት ላይ ባወጣው የእስር ማዘዣ ነው ኮንግረሱ ማዕቀቡ እንዲጣልበት የወሰነው፡፡
በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ ብራየን ማስት የአለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን “የካንጋሮ ፍርድ ቤት” ሲሉ ወርፈውታል፡፡
ለድምጽ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በ243 ድጋፍ በ140 ተቃውሞ የጸደቀ ሲሆን በቀጣይ ሪፐብሊካኖች በርካታ ወንበር ወደ ያዙበት ሴኔት ተዘዋውሮ ድምጽ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትሩን ጨምሮ 3 ከፍተኛ የሀማስ ባላለስልጣናትን በጦር ወንጀል በመክሰስ ፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ ያወጣው በህዳር ወር ነበር፡፡
በወቅቱ ኔታንያሁ “እስራኤል በአለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት የቀረበባት ክስ የማይረባ እና ከፖለቲካ ውግንና የተነሳ ነው” በሚል ውድቅ አድርገውታል።
አይሲሲ በሮም ስምምነት የተካተቱ አባላት ንቁ ተሳትፎ ሳያደርጉ ህጋዊ ውሳኔዎቹን የሚያስፈጽምበት ምንም አይነት መንገድ የለውም።
እስራኤል፣ ልክ እንደ አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና ለፍርድ ቤቱ ስልጣን እውቅና አልሰጠችም፡፡