“ከሞቱ ሰዎች ጋር መነጋገር” የሚያስችለው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ
ቴክኖሎጂው የሟቾችን መልክ፣ ድምጽ እና ሌሎች ባህሪያት የተላበሰ “የሰው ልጅ ዲጂታል ኮፒ ነው” ተብሏል
ባለሙያዎች “ከሞተ ሰው ጋር መነጋገር” ሊያስከትል የሚችለውን ስነልቦናዊ ጉዳት ማጤን ያስፈልጋል ብለዋል
በጣም የምንወደውን እና መተኪያ የሌለውን የቅርባችን ሰው በሞት መነጠቅ ለረጅም ጊዜ ብርቱ ሀዘን ጥሎ ማለፉ አይቀርም።
ከመልካም ትዝታው ጋር ከመኖር ውጭም ምንም አማራጭ አልነበረንም።
የረቀቁ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ባለሙያዎች ግን “ለምን በትዝታ ብቻ ትኖራላችሁ? በሞት የተለዩዋችሁን ሰዎች በህይወት ያሉ ያህል እንዲሰማችሁ ማድረግ እንችላለን፤ ልታወሯቸውም ትችላላችሁ” እያሉ ነው።
የሟቾቹን መልክ፣ የሰውነት ቅርጽ፣ ድምጽ፣ አረማመድ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች በሙሉ የተላበሰ ወይም “የሰው ልጅ ዲጂታል ኮፒ” ነው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት የተፈጠረው።
ይህም የሟቹ ፎቶግራፎች፣ የድምጽ እና ቪዲዮ መልዕክት ልውውጦች ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ተወስደው እንደሚቀነባበር የኪዊንስ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው ጥናት አመላክቷል።
በዩኒቨርሲቲው የኦስተን የህግ ኮሌጅ ተመራማሪዎች ይህ “የሞተን ሰው በዲጂታል መንገድ ዳግም የመመለስ” ጥረት በሟች ቤተሰቦች ላይ ሀዘን ከማበርታት ውጭ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ያነሳሉ።
ድምጽ እና መልኩን ከምናውቀውና ግን አልቅሰን ከቀበርነው ሰው አምሳያ ወይም “ዲጂታል ኮፒው” ጋር ለመነጋገር መሞከር ሊያስከትል የሚችለው የስነልቦና ችግርም በቀጣይ ሊጠና እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ እንዲህ “ከሞቱ ሰዎች ጋር ላነጋግራችሁ” ከማለቱ ቀደም ብሎም ማይሄሪቴጅ የተሰኘው ድረገጽ በ2021 የሞቱ ሰዎችን ፎቶግራፍ ወደ ተንቀሳቃሽ ምስል መቀየር የሚያስችል አገልግሎት ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።