በኢትዮጵያ የዩኤኢ ኤምባሲ ባለስልጣን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ጉብኝት አድርገዋል
ኢትዮጵያ እና ዩኤኢ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ተወያዩ
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር የመሥራት ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የአገሪቷ ኤምባሲ ገለፀ።
በኢትዮጵያ የዩኤኢ ኤምባሲ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ እና የሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ታላል አል-አዚዚ እና የኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ውይይት ባደረጉበት ወቅት ሀገራቱ በዘርፉ መተባበር የሚያስችሏቸው ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል መክፈቷ ለሀገሪቱ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ለልማቷ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ታላል አል-አዚዚ ገልጸዋል። የግብርና፣ የጤና፣ የፋይናንስና የትራንስፖርት ዘርፎችን በቴክኖሎጂ ለማዘመንም የማዕከሉ መከፈት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።
በልማት ፖሊሲያቸው ለአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ቅድሚያ ከሰጡ የዓለም ሀገራት መካከል ዩኤኢ ግንባር ቀደም መሆኗን የጠቆሙት ታላል አል-አዚዚ እስከ 2031 የሚዘልቅ የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ ስትራቴጂ መቅረጿንም ነው የገለጹት፡፡
ዩኤኢ የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሾመች የዓለማችን የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን በቀጣናው የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዩኒቨርሲቲ የከፈተች ቀዳሚ አገር እንደሆነችም ተናግረዋል፡፡
በሞሃመድ ቢን ዛይድ ስም የተሰየመው ዩኒቨርሲቲው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ተማሪዎች በአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ- ግብር እንደሚሰጥም በውይይቱ ወቅት አል-አዚዚ ጠቁመዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና ኢትዮጵያ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ትብብሮች በመጥቀስ ፣ ሀገራቱ በአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ ዘርፍም መተባበር የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን አል-አዚዚ አብራርተዋል፡፡
የዩኤኢ ኤምባሲ የኢትዮጵያ የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከልን መጎብኘቱን ያደነቁት ኢንጂነር ወርቁ ስለ ማዕከሉ አመሰራረት፣ ስለሚሰራቸው ሥራዎችና ግቡን በተመለከተ ለታላል አል-አዚዚ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ማዕከሉ እንዲመሰረት ዩኤኢ ስላደረገችው ድጋፍም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይነት መተባበር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ሁለቱ አካላት ተስማምተዋል፡፡