“አልባ ሬናይ” በስፔን ቴሌቪዥን ጣቢያ ስራ አገኘች
ቆንጆዋ የዲጂታሉ አለም ተጽዕኖ ፈጣሪ የኢንስታግራም እና ቲክቶክ ተከታዮቿን በቴሌቪዥን ፕሮግራም ጠብቁኝ ብላለች
አልባን የፈጠረው ኩባንያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቷ የጋዜጠኞችን ስራ እንደማትነጥቅ አስታውቋል
በኢንስታግራምና ቲክቶክ ዝነኛ የሆነችው አልባ ሬናይ ወደ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ልትል መሆኑን አብስራለች።
የታዋቂውን “ሰርቫይቨር” የቴሌቪዥን ፕሮግራም የስፔን ቅጂ ላይ ልዩ ፕሮግራም እንደምትመራም ለአድናቂዎቿ ገልጻለች።
አልባ ሬናይ ወብ መልክና ቁመና አላት ግን የውሸት ነው።
ባለፈው አመት የግዙፉ ሚዲያሴት ቴሌቪዥን አጋር በሆነው “ቢ ኤ ላየን” የተፈጠረችው አልባ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤት ናት።
350 ሰዎች ምን አይነት አካላዊ ውበትና ቁመና እንደሚመርጡ ተጠይቀው የተፈጠረችው አልባ ሬናይ በኢንስታግራም እና ቲክቶክ በርካታ ተከታዮችን ለማፍራት ግን ጊዜ አልወሰደባትም።
ባለፈው ሳምንት በሴኑ ቴሌሲኖ ቴሌቪዥን ጣቢያ ልዩ ፕሮግራም እንደምትመራ ማሳወቋም ትኩረት ስቧል።
አድናቂዎቿም በቴሌቪዥን ፕሮግራሟ ስኬት እንዲቀናት ተመኝተውላታል፤ አንዳንዶቹ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የምትጠቀም ግዑዝ መሆኗን እስከመዘንጋት መድረሳቸውንም ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
በቻይና፣ ጃፓን እና ሌሎች የእስያ ሀገራት የሮቦት ዜና አንባቢዎችን ወደ ስራ ማስገባት ተጀምሯል።
ይህም ሮቦቶች የሰው ልጆችን ስራ እንዲነጥቁ ያደርጋል የሚል ትችት ሲያስነሳ መቆየቱ ይታወሳል።
አልባ ሬናይን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቋንቋ ጋር ያግባባት “ቢ ኤ ላየን” የተሰኘው ኩባንያ በበኩሉ አልባ የምትነጥቀው የሰው ልጅ ስራ አይኖርም በሚል ተከላክሏል።
በአልባ ፕሮጀክት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ባለሙያዎች፣ መሀንዲሶችና ፊልም ሰሪዎችን ጨምሮ 32 ሰዎች እንደሚሳተፉ በመጥቀስም ለበርካቶች የስራ እድል ፈጠረች እንጂ የሰው ልጆችን ስራ አልቀማችም ብሏል።
ከወቀሳና ስጋቱ ይልቅ በሚዲያው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ዘመኑ ከሚፈልገው ቴክኖሎጂ ጋር ማስተዋወቅ ግድ እንደሚልም ነው ያሳሰበው።
አልባ ሬናይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲጂታሉ አለም ተቀባይነትን ካተረፉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶች አይታና ሎፔዝ እና ሌክሲ ሎቭ ጋር ተመድባለች።
በርካታ መገናኛ ብዙሃንም የማይደክሙትን እና ወጪ ይቀንሳሉ ተብለው የታመኑትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዜና አንባቢ እና ፕሮግራም አቅራቢዎች ወደ ስራ ለማስገባት በስፋት እየሰሩ ነው ተብሏል።