ትክክለኛውን እድሜያችን የሚናገርውና “እርጅናን የሚያስቀረው” ቴክኖሎጂ
ተመራማሪዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት በመጠቀም በቤት ውስጥ በቀላሉ እድሜያችን የምናውቅበትን ቴክኖሎጂ አስተዋውቀዋል
እያረጁ ያሉ የሰውነታችን ክፍሎች እና ህዋሳትን ለይቶ ያሳያል የተባለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት፥ ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችንም በዝርዝር ያስቀምጣል ተብሏል
በሳይንስ ልብወለዶች ይንጸባረቅ የነበረውን “ጊዜን ባለበት የማስቆም” ጉዳይ እውን ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች ቀጥለዋል።
የሰው ልጅን ለእርጅና የሚዳርጉ ጉዳዮችን ለይቶ መፍትሄ ይሰጣል የተባለ አዲስ ቴክኖሎጂም በይፋ መተዋወቁ ነው የተነግረው።
ሰዎች ወላጆቻቸውን መጠየቅ ሳይገባቸው ትክክለኛ እድሜያቸውን በቤታቸው ውስጥ የሚያውቁበት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሚጠቀም ቴክኖሎጂ በታሊ ሄልዝ እና ሌሎች አጋሮቹ በኩል ተዋውቋል።
የደም፣ የሽንት እና የምራቅ ናሙናዎችን ተቀብሎ የሰውነታችን ክፍሎች፣ ህብረ ህዋስ እና ህዋሳት ስራቸውን የሚፈጽሙበትን ፍጥነት የሚያመላክተው ቴክኖሎጂ፥
እቅጩን እድሜ ከመናገር ባለፈ እርጅናን የሚያስቀሩ ምክሮችን ለእያንዳንዱ ደንበኛ ያቀርባል ተብሏል።
ላለፉት 13 አመታት በአይጦች ላይ ምርምር ያደረገው ታሊ ሄልዝ ፥ እያንዳንዱ ህዋሳት የት፣ ምን እና እንዴት ነገሮችን መፈጸም እንዳለባቸው የሚወስነውን “ኤፐጂኖም”፥ መቆጣጠርና ወደቀደም ይዞታው መመለስ ተችሏል ብሏል።
ይህ ምርምርም በሰው ልጆች ላይም እንደሚሰራ በምርምር መረጋገጡን ነው የታሊ ሄልዝ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሜላኒ ጎልዲ የተናገሩት።
የታሊ ሄልዝ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሚጠቀም ቴክኖሎጂ “ታሊኤጅ ክሎክ” ይሰኛል።
“ታሊኤጅ ክሎክ” ከ8 ሺህ በላይ የዘረመል ናሙናዎች ላይ የተደረጉ ምርምሮችን የያዘ ነው።
የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎችም ናሙናቸውን በዚሁ ቴክኖሎጂ በማስገባት እድሜያቸውን የሚወስኑ ህዋሳት ጤናን ማወቅና መፍትሄዎቹንም መረዳት ይችላሉ ተብሏል።
ደንበኞችም በወር እስከ 129 ዶላር በመክፈል ለአመት ወይም ለስድስት ወር አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ነው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የገለጹት።
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ዶክተር ዴቪድ ሲንክሌር፥ ዘረመል በህይወት የመቆየት እድላችን ብቸኛ አመላካች አይደለም ብለዋል።
90 በመቶ በህይወት የመቆያ እድሜያችን የሚወሰነው በእለት ተዕለት አኗኗራችን ነው የሚሉት ዶክተር ዴቪድ፥ ቀጣዩ የምርምር ትኩረትም በዚሁ ላይ እንሚያተኩርና የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚጠቀሙ ቴክኖሎጂዎችም ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጅን በህይወት የመኖሪያ ጊዜ ከፍ ለማድረግ የሚካሄዱ ምርምሮች የቀጠሉ ሲሆን፥ ለምርምሮች የሚወጣው ወጪም እየጨመረ ነው።
በ2025 እድሜን ማርዘም ላይ ያተኮሩ የቴክኖሎጂ ስራዎች የ2 ነጥብ 7 ትሪሊየን ዶላር ዋጋ እንደሚኖራቸውም ነው የዴይሊ ሜል ዘገባ የሚያሳየው።