ለስኳር ታማሚዎች ይጠቅማል የተባለው አዲሱ የአፕል ስማርት የእጅ ሰዓት
ኢ5 የተባለው የእጅ ሰዓት ያለ ናሙና ምርመራ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ይለካል
የፈጠራ ስራው ላለፉት 12 ዓመታት ምርምር ሲደረግበት እንደቆየ ተገልጿል
አፕል ኩባንያ ለስኳር ህመምተኞች ጠቀሜታ ያለው የእጅ ሰዓት መስራቱን ገለጸ።
ብስቲቭ ጆብስ የተቋቋመው አፕል የቴክኖሎጂ ኩባንያ በተለይም ለስኳር ህመምተኞች የሚሆን የእጅ ሰዓት መስራቱን አስታውቋል።
እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ከሆነ ይህ አዲስ ፈጠራ በእጅ ሰዓት መልክ የተሰራ ሲሆን ያለ ደም ናሙና በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መለካት ይችላል።
ላለፉት 12 ዓመታት ምርምር ሲደረግበት የቆየው ይህ ቴክኖሎጂ ኢ5 የሚል መጠሪያ እንደተሰጠውም ተገልጿል። በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ማዕከሉን ያደረገው አፕል ኩባንያ አዲስ ፈጠራውን በቅርቡ ለገበያ አቀርባለሁ ብሏል።
ይሁንና አፕል ኩባንያ ይህን አዲስ የእጅ ሰዓት በምን ያህል ዋጋ ለገበያ እንደሚቀርብ ለጊዜው ከመናገር ተቆጥቧል።
ይህ የእጅ ሰዓት አስቀድመው የስኳር ህመምተኛ መሆናቸውን ካወቁ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችም በደማቸው ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን እንዲያውቁ እና እንዲጠነቀቁ ያደርጋልም ተብሎለታል።
ይህ ሰዓት በእጅ ላይ ሲታሰር በደም ስራችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠንን መለካት የሚያስችለው ቴክኖሎጂ እንዳለውም ተገልጿል።
ኩባንያው ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች አዳዲስ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ከጥቂት ወራት በኋላ ለደንበኞቹ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል።