ከ92 ዓመት በኋላ የሰው ልጅ ስራዎች ሙሉ ለሙሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ይተካሉ ተባለ
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከወዲሁ ቁጥጥር እንዲደረግበት ባለሙያዎች እየወተወቱ ናቸው
በ2116 የሰው ልጆች ሙሉ ለሙሉ ስራ አጥ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ትንበያውን አስቀምጧል
ከ92 ዓመት በኋላ የሰው ልጅ ስራዎች ሙሉ ለሙሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ይተካሉ ተባለ፡፡
በየጊዜው የሚፈጠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ህይወትን እያቀለሉ እና እያዘመኑ መጥተው አሁን አለንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ዓለም አዳዲስ ቴክኖሎጂ ስራዎችን እያበረታታች ስትመጣ ቆይታ አሁን ላይ ደግሞ በነዚህ ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ምክንያት የሰው ልጆች ህይወት ከማቅለል ወደ ማክበድ እየገባ ይገኛል፡፡
በተለይም ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት የተባለው ፈጠራ ከዚህ በፊት ይታሰቡ የማይመስሉ ስራዎችን ማከናወን ተችሏል፡፡
ይህ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጆችን ተፈላጊነት፣ ስሜት እና ፍላጎት በመቀነስ እንደ ግኡዝ እቃ እንዲታይ የሚያደርግ እንደሆነ ባለሙያዎች በመናገር ላይ ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ባወጣው ጥናት ከ92 ዓመት በኋላ ማለትም በ2116 ላይ የሰው ልጆች ስራ ሙሉ ለሙሉ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ይተካል ሲል ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
በኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ፊሊፕ ቶር እንዳሉት "አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ማን እንደሚቆጣጠረው መታወቅ አለበት፣ ይህ ካልሆነ እና ሁሉም ሰው ቴክኖሎጂውን ካወቀ ለዓለማችን አደጋ ነው፣ የሰው ልጆችን የመስራት ፍላጎትን በመግደል ሊያጠፋን ይችላል" ብለዋል፡፡
አፍሪካ ለማይቀርላት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትኩረት ልትሰጥ እንደሚገባ ተጠቆመ
አይኤምኤፍ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም አይ የሰው ልጆን 40 በመቶ ስራ ሊነጥቅ ይችላል ማለቱ ይታወሳል፡፡
የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክርስታሊና ጆርጂየቫ “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) የሰው ልጆችን ስራ ከመንጠቅ ባሻገር ኢፍትሃዊነትን ያባብሳል” ብለዋል።
ሀገራት ይህን ለሰው ልጆች አደጋ ሊሆን ይችላል የተባለውን ቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር ህግ እና ደንቦችን በማርቀቅ ላይ ሲሆኑ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎችም ህግ አውጥተዋል፡፡
የበለጸጉት ሀገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ይዞት ከመጣው በረከት በብዙው ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ቢጠበቅም ሚሊየኖች ከስራ ገበታቸው ሊሰናበቱ ይችላሉ የሚሉ ጥናቶች በተደጋጋሚ ወጥተዋል።