በጦርነት መካከል ለተቸገሩ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ የሚያደርሱት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሮቦቶች
ተመድ ምግብና ሌሎች የእርዳታዎችን በሮቦት የማጓጓዝ ስራው በቀጣይ ዓመት ይጀመራል ተብሏል
ተመድ ሮቦቶችን ለመጠቀም የወሰነው በጦርነት መካከል የሚሞቱ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች ቁጥር ማሻቀቡን ተከትሎ ነው
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሮቦቶች በመጠቀም ወደ ጦርነት ቀጠናዎች እርዳታ የማድረስ ስራ ሊጀምር መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።
በሮቦቶች ተጠቅሞ በጦርነት እና በተፈጥሮ አደጋ ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ምግብ እና ወሳኝ የሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ ስራው በቀጣይ የፈረንጆቹ ዓመት እንደሚጀመር የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሃላፊዎች ነግረውኛል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
- በዓለማችን 690 ሚሊየን ሰዎች እራት ሳይበሉ ለመተኛት ይገደዳሉ- የዓለም ምግብ ፕሮግራም
- ፑቲን የዩክሬን ወደቦችን ለእህል ጭነት ክፍት እንዲያደርጉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጠየቀ
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በግጭቶች መካከል በሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።
በሱዳን በቅርቡ በተጀመረው ጦርነት ብቻ 3 የተመድ የምግብ ፕሮግራም ሰራተኞች መገደላቸውንም የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።
የተመድ የምግብ ፕሮግራም የኢኖቬሽን ሃላፊ ብረንሃርድ ኮዋተስች፣ አንዳንዴ በጣም አስቸጋሪ ቦታዎች ላይ የምግብ ፕሮግራም አሽከርካሪዎችን መላክ ከባድ ሊሆን ይችላል፣ በዚህ ጊዜ ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ ነው ብለዋል።
ለዚህም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚሰሩ ሮቦት መኪናዎችን መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ሃላፊው፣ መኪናዎቹ በቀጣይ ዓመት ወደ ስራ ይገባሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
የእርዳታ እህል ጫኝ መኪናዎቹ ከ1 እስከ 2 ቶን ድረስ የእርዳታ እህል እና ቁሳቁስ የመጫን አቅም አላቸው ተብሏል።
መኪናዎቹ ከዚህ ቀደም ከፈረንጆቹ 2012 እስከ 2016 ድረስ በሙከራ ደረጃ በሶሪያ ጥቅም ላይ ውለውም ነበር።