የረድኤት ድርጅቶች የሊቢያ ጎርፍ ተጠቂዎች በጅምላ እንዳይቀበሩ ጠየቁ
በምስራቅ ሊቢያ ዕሁድ በደረሰው የጎርፍ አደጋ በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አልፏል
ድርጅቶቹ የጅምላ ቀብሩ ለሟች ቤተሰቦች የአእምሮ መረበሽ ያስከትላል ብለዋል
የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ በርካታ የረድኤት ድርጅቶች የሊቢያ ጎርፍ ተጠቂዎች በጅምላ እንዳይቀበሩ የሀገሪቱ ባለስልጣናትን ጠይቀዋል።
ድርጅቶቹ ይህን ያሉት አንድ ሽህ የሚሆኑ የአደጋው ተጎጂዎች አንድ ላይ በጅምላ መቀበራቸው ከተሰማ በኋላ ነው።
ዕሁድ ዕለት በምስራቅ ሊቢያ ሁለት ግድቦች በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ከተደረመሱ በኋላ ደርና ከተማን ጠራርጎ ወስዷል።
በጎርፍ አደጋው በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ ሌሎች በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የገቡበት አልታወቀም ተብሏል።
በዓለም የጤና ድርጅት በኩል በጋራ የወጣው መግለጫ ሟቾችን በችኮላ በጅምላ መቅበር እንዲያበቃ ጠይቋል።
መግለጫው ቀብሮች በሰነድ በመደገፍ የተሻለ ስርዓት ሊበጅላቸው ይገባል ብሏል።
የችኮላ ቀብሮች ለሟች ቤተሰቦች ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የአእምሮ መረበሽ እንደሚያስከትል የጠቀሱት የረድኤት ድርጅቶች፤ ማህበራዊና ህጋዊ ችግሮችንም ይደቅናል ሲሉ ተናግረዋል።
በተፈጥሮ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስከሬን በአብዛኛው የጤና ስጋት ባይደቅንም፤ አስከሬን ስለሚፈራርስ የውሃ ምንጭ ላይ ብክለት ሊያስከት ይችላልም ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ሀሙስ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው በደርና ከተማ አንድ ሽህ አስከሬንና በአልበይዳ አካባቢ 100 አስከሬን በጅምላ ተቀብረዋል።