በሊቢያ በ15 ስደተኞች ላይ አሰቃቂ ግዲያ መፈጸሙን ተመድ ገለጸ
በያዝነው ዓመት ብቻ 216 ሰዎች የሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ መሞታቸው የአይ.ኦ.ኤም መረጃ ያመለክታል
ግዲያው በተቀናቃኝ አዘዋዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የተፈጸመ ሊሆን ይችላል ተብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሊቢያ በ15 ስደተኞች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግዲያ አወገዘ።
ድርጊቱ ጥገኝነት ጠያቂዎች ምንም አይነት ዋስታና እንደሌላቸውና ጥበቃ እንደማይደረግላቸው የሚያሳይ ነው ብሎታል ተመድ ባወጣው መግለጫ።
ባለፈው አርብ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ ወደ ጣሊያን የባህር ዳርቻ ለመድረስ ለሚፈልጉ አስፈላጊ መነሻ በሆነችው በሊቢያዋ ሳብራታ የባህር ዳርቻ 15 አስከሬኖች መገኘታቸው ተገልጿል።
ነገሩ አሰዛኝ የሚያደርገው ደግሞ የተገኙት አስከሬኖች 11ዱ የተቃጠሉ እንዲሁም አራቱ ከተቃጠለችው ጀልባ ተጥለው የተገኙ መሆናቸው ነው ተብሏል፡፡
የሊቢያ ባለስልጣናት ሁሉንም ወንጀለኞች ለማምጣት ፈጣን ፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ አንዲያደርጉ አጥብቆ ያሳሰበው የተመድ “ትክክለኛው ሁኔታ ገና በትክክል ባይታወቅም ግዲያው በተቀናቃኝ አዘዋዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የተፈጸመ ሊሆን ይችላል” ብሏል።
ይህ አሳዛኝ ክስተት "በሊቢያ ውስጥ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚያጋጥሟቸውን ከለላ እጦት እንዲሁም በአደገኛ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና የወንጀል መረቦች የሚፈጸሙትን ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መኖሩ የሚያሳይ ነው" ሲልም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የገለጸው።
የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት፤ ፍልሰተኞቹ በአብዛኛው ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ናቸው፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2011 የሙዓመር ጋዳፊን መንግስት መውደቅ ተከትሎ የተፈጠረው ትርምስ ሊቢያን ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ፣ የአረብ ሀገራት እና ከደቡብ እስያ በጣሊያን በኩል አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመድረስ ለሚጓጉ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ተመራጭ መንገድ አድርጓታል።
እነዚህ ስደተኞች አደገኛውን የሜዲትራኒያን ባህር ለማቋረጥ ሲሞክሩ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ እንደሚወድቁና በዚህም ለተለያየ አደጋ እንደሚጋለጡም የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 14 ሺህ 157 ስደተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ሊቢያ መመለሳቸው እንዲሁም ቢያንስ 216 ሰዎች ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ መሞታቸው የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
እንደፈረጆቹ ጥቅምት 3 ቀን 2013 በርካታ ኤርትራውያን የሚገኙባቸው 350 ስደተኞች በላምፐዱሳ ባህር ዳርቻ የሞቱበት አሳዛኝ አደጋ አይዘነጋም። አደጋው ከደረሰ ባሳለፍነው ሳምንት 9 ዓመት ሆኖታል።