በሊቢያ ደርና ከተማ ብቻ በጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 20 ሺህ ሊደርስ ይችላል ተባለ
በደርና ከተማ ግድብ ተደርምሶ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የገቡበት አይታወቅም
ሊቢያ በተለያዩ ከተሞች በደረሰ የጎርፍ አደጋ እስካሁን 5000 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል
በሊቢያ የተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ በደርና ከተማ ብቻ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር እስከ 20 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል የከተማዋ ከንቲባ አስታወቁ።
ሊቢያ የደረሰውና “ዳንኤል” የሚል ስያሜ የተሰጠው ማእበልን ተከትሎ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ቤንጋዚ፣ አል ባይዳ፣ አል ማርጅ እና ደርና የተሰኙት ከተሞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው።
የሊቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ታሬክ አል-ካራዝ ፤ በሊቢያ በተለያዩ ከተሞች በደረሰው የጎርፍ አደጋ እስካሁን የ3 ሺህ 840 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን እና ከእነዚህም ውስጥ የ3 ሺህ 190 ሰዎች አስክሬን መቀበሩን አስታውቀዋል።
በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ 400 ሰዎች የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውን ያስታወቁት ቃል አቀባዩ፤ ከእነዚህም ውስጥ እበዛኞቹ የሱዳን እና የግብጽ ዜጎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሊቢያ የሲቪል አቪዬሽን ሚኒስትር ሂቸም አቡቸኪዋት በበኩላቸው በጎርፍ አደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ5 ሺህ 300 በላይ መድረሱን እና ቁጥሩ በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል አስታውቃል።
ደርና በተባለች ከተማ ደግሞ ባሳለፍነው ማክሰኞ ሁለት ግድቦች እና አራት ድልድዮች መደርመሳቸውን ተለትሎ በ10 ሺህ ሰዎች የገቡበት አይታወቅም ተብሏል።
የደርና ከተማ ነዋሪዎች እና የነፍስ አድን ሰራተኞች በጎርፍ ተወስደው ደብዛቸው የጠፋ ቤተሰቦቻቸውን እና ዘመዶቻቸውን በማፈላለግ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
የደርና ከተማ ከንቲባ አብዱልሜናም አል-ግሃይቲ፤ በጎርፍ አደጋው ክፉኛ በተጎዳቸው ደርና ከተማ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ18 ሺህ እስከ 20 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል አስታውቀዋል።
በሊቢያ ባሳለፍነው እሁድ ድንገት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ድልድዮችን እና ህንጻዎችን የገነደሰ ሲሆን፤ በተለይም የምስራቃዊቷን ደርና ከተማ ሩብ ክፍል አውድሟል ተብሏል።
125ሺ ነዋሪዎች ያሉባት የምስራቋ ደርና ከተማ የፈራረሱ መንደሮች፣ የተደረመሱ ህንጻዎች፣ የተገለበጡ መኪናዎችን እንዲሁም የድልድይ ፍርስራሽ ማየቱን ሬውተርስ ጋዜጠኛውን የአይን እማኝ አድርጎ ዘግቧል።