በአየር ብክለት ምክንያት በየአመቱ 7 ሚሊየን ሰዎች ይሞታሉ - ጥናት
ማሊ፣ ናይጀሪያ፣ ኮቲዲቯር እና ጋና የአየር መበከል አሳሳቢ ደረጃ የደረሰባቸው ሀገራት መሆናቸው ተገልጿል
99 በመቶ የአለም ህዝብ በአለም ጤና ድርጅት መመዘኛ መሰረት “የቆሸሸ” አየርን ይተነፍሳል
የአየር ብክለት በየአመቱ የ7 ሚሊየን ሰዎችን ህይወት እንደሚቀማ የአለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።
ከአለማችን ህዝብ 99 በመቶው በአለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት “የቆሸሸ” አየርን ይተነፍሳል።
የአተነፋፈስ ስርአትን አዛብቶ ለሳንባ ካንሳር፣ ለልብ ህመምና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የሚያጋልጠው የአየር ብክለት “በዝምታ ገዳይ” ሆኖ ቀጥሏል።
በላንሴት ጆርናል ላይ የወጣው ጥናትም በአየር ብክለት ምክንያት ለካንሰር የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን አመላክቷል።
ከፋብሪካዎች የሚለቀቅ ካርበን እንዲቀንስ ትግሉ ቢቀጥልም የደን ጭፍጨፋ እና ቃጠሎው አልቆመም፤ የሃይል ፍላጎቱም በብዙ እጥፍ እየጨመረ ነው።
መጠኑ ይለያይ እንጂ በአየር ብክለት ተጎጂ የማይሆን የአለማችን ክፍል የለም።
ማሊ፣ ናይጀሪያ፣ ኮቲዲቯር፣ ቶጎ እና ጋና የአየር ብክለት ክፉኛ እየፈተነን ነው ያሉ ሀገራት ናቸው።
ሀገራቱ ለመንግስታቱ ድርጅት ባቀረቡት እቅድ የአየር መበከልን መቀነስ ዋነኛ የአየር ንብረት ጥበቃ ስራቸው ትኩረት መሆኑን አመላክተዋል።
የአለማቀፉ የአየር ንብረት እና ጤና ጥምረት ባወጣው ጥናት በተበከለ አየር ከሚጠቀሱት ቀዳሚ 15 ሀገራት 14ቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ናቸው ይላል።
ጥናቱ የአየር መበከል ከሁለት ሶስተኛ በላይ የአለም ሀገራት ላይ የጤና ችግር እየፈጠረ መሆኑንም ጠቁሟል።
የመንግስታቱ ድርጅትም ሀገራት በቤት ውስጥም ሆነ የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ ሀገራት የተለየ እቅድ ነድፈው እንዲሰሩ አሳስቧል።