የኤርባስ ሰራተኞች ገናን ካከበሩ በኋላ መታመማቸው ተገለጸ
የኩባንያው ሰራተኞች በፈረንሳይ ናንትስ ከተማ ገናን ካከበሩ በኋላ ማስታወክ እና ተቅማጥ አጋጥሟቸዋል ተብሏል
የምግብ መመረዝ ሳያጋጥም እንዳልቀረ የገመተው ኩባንያው ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል
የኤርባስ ሰራተኞች ገናን ካከበሩ በኋላ መታመማቸው ተገለጸ።
የዓለማችን ግዙፉ የአቪዬሽን ተቋም የሆነው ኤርባስ ሰራተኞች የገና በዓልን በፌሽታ አሳልፈዋል።
700 ገደማ ይሆናሉ የተባሉት እነዚህ ሰራተኞች ግን በዓሉን አክብረው ወደ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ህመም እንዳጋጠማቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ሰራተኞቹ የገና በዓልን ደመቅ ባለ መልኩ በጋራ ባከበሩበት ወቅት የተመገቡት ምግብ ለህመም ሳይዳርጋቸው እንዳልቀረ ተገልጿል።
እነዚህ ሰራተኞችም ተቅማጥ፣ ማስታወክ እና ከሆድ እቃ ጋር የተያያዙ ህመሞች አጋጥሟቸውል ተብሏል።
ለሰራተኞቹ የገና በዓል ፕሮግራም ያዘጋጀው ኤርባስ በበኩሉ ለበዓሉ የተዘጋጁ ምግቦች እና መጠጦች ሳይመረዙ እንዳልቀሩ ተናግሯል።
ሰራተኞቹ ያጋጠማቸውን ህመም ተከትሎ ለሁለት ቀናት ከስራ ቀርተዋል የተባለ ሲሆን በሁዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ በመደረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
ድርጅቱ በበይነ መረብ አማካኝነት በበዓሉ ላይ ለተሳተፉ ሰራተኞች በላከው አስተያየት መሰብሰቢያ ቅጽ መሰረት አብዛኞቹ ከፍየል ወተት የተሰራ ቺዝ መመገባቸው ለህመማቸው መነሻ ሳይሆን እንዳልቀረ ተናግረዋል ተብሏል።
ኤርባስ ኩባንያ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ጥምረት የተመሰረተ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ተቋም ሲሆን በአምስት ሀገራት ባሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከ150 ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉት።