ቻይና ቦይንግን ጨምሮ በአሜሪካ ኩባንያ ምርቶች ላይ እገዳ መጣሏ ለኤርባስ አዲስ እድል ፈጥሮለታል ተብላል
ቦይንግ ከቻይና ገበያ እየቀዘቀዘ ሲሄድ ኤርባስ ገበያውን እየተቆጣጠረ መምጣቱ ተገለጸ።
የአሜሪካው ግዙፉ የአቪዬሽን ኩባንያ ቦይንግ በቻይና ያለውን ገበያ እያጣ መምጣቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቦይንግ ኩባንያ በአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት መካረር ምክንያት ገበያው እንደተጎዳበት አስታውቋል።
በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መበላሸት ምክንያትም ቦይንግ ኩባንያ ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ ከቻይና የአውሮፕላን ግዢ ጥያቄ እንዳልቀረበለት ተገልጿል።
- ቦይንግ ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ በታዳሽ ሀይል የሚሰሩ አውሮፕላኖችን እንደሚያመርት አስታወቀ
- ሩሲያ የቦይንግ እና ኤርባስ ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ መጠቀም እንደምታቆም አስታወቀች
ይህን ተከትሎም ኤርባስ የቻይናን አቪዬሽን ገበያ እየተቆጣጠረ ነው ተብሏል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮንደርሊን ቻይናን በጎበኙበት ወቅት ኤርባስ ተጨማሪ መገጣጠሚያ እንዲከፍት ስምምነት መፈረሙ ተገልጿል።
የቻይና አቪዬሽን ገበያ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ሲሆን በቀጣዮቹ ዓመታት የዓለም አቪዬሽን እድገት ውስጥ የ20 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።
ቻይና ከኤርባስ 160 አውሮፕላን ለመግዛት አዲስ ስምምነት መፈራረሟም ተገልጿል።
ይሁንና ቦይንግ ኩባንያ በዚህ ዓመት አንድ አውሮፕላን ብቻ ለቻይና አስረክቧል የተባለ ሲሆን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ማዕቀብ ሲጥሉ ቻይናም እንደ ቦይንግ ባሉ የዋሽንግተን ኩባንያዎች ላይ እገዳ ጥላለች።
የአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት መሻሻሎችን ከማሳየት ይልቅ በየጊዜው እየተካረረ ሲሆን በተለይም የታይዋን ጉዳይ፣ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ፣ የቴክኖሎጂ ፉክክር እና አፍሪካን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች ለግንኙነቱ መሻከር ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።