አለምአቀፉ ኤየርፖርት ሰዎች ተቃቅፈው የሚቆዩበትን ጊዜ ገደበ
አየርመንገዱ ሰዎች የሚወዷቸውን ለመሰናበት ሶሰት ደቂቃ በቂ ነው የሚል ህግ አውጥቷል
አየር መንገዱ ይህን ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቷል
አለምአቀፉ ኤየርፖርት ሰዎች ተቃቅፈው የሚቆዩበትን ጊዜ ገደበ።
ኒውዝላንድ ውስጥ የሚገኘው ዱነዲን አለምአቀፍ ኤየርፖርት ሰዎች ተቃቅፈው በሚቆዩበት የጊዜ መጠን ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሎ ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጥሯል።
ኤየርፖርቱ ሰዎች የሚወዷቸውን ለመሰናበት ሶሰት ደቂቃ በቂ ነው የሚል ህግ ያወጣ ሲሆን ጥቂቶች እርምጃውን "ኢሰብአዊ" ሲሉ ገልጸውታል።
ከደቡባዊቷ ዱነዲን ከተማ 27 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በቀዝቃዛነቱ በሚታወቀው በዚህ ኤየርፖርቱ መንገደኞች በሚሰነባበቱበት ቦታ "ከፍተኛው ተቃቅፎ የመቆያ ጊዜ ሶሰት ደቂቃ ብቻ ነው" የሚል ማስታወቂያ ተተክሏል። ማስታወቂያው "ረዘም ላለ መተቃቀፍ ወይም ስንብት የፓርኪንግ ወይም የመኪና ማቆሚያ ቦታውን ይጠቀሙ" የሚል ማስጠንቀቂያም አካቷል።
ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተደበላለቀ አስተያያት እየሰጡ መሆናቸውን ዴይሊሜይል ዘግቧል።
ጥቂቶች ውሳኔው የሰዎችን የስንብት ጊዜ ይገድባል ያሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የመንገደኞችን እንቅስቃሴ ምቹ የሚያደርግ እና እንደትምህርት ቤት ባሉ ተቋማት ሊተገበር የሚገባው ነው ሲሉ እርምጃውን ደግፈውታል።
የኤየርፖርቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳኒኤል ዲ ቦኖ የሚወዷቸውን ሰዎች ለመሰናበት ሶሰት ደቂቃ በቂ መሆኑን እና ረጅም ጊዜ በመንገደኞች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ሲሉ የአርመንገዱን ውሳኔ ተገቢነት ደግፈዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት "ኦክሲቶሲን" የተባለውን የፍቅር ሆርሞን ለማመንጨት 20 ሰከንድ በቂ እንደሆነ ጥናት ማረጋገጡን አመልክተዋል። ያም ሆኖ ውሳኔው በሰዎች ሰሜት ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚለው ጥያቄ ማነጋገሩን ቀጥሏል።